የወላይታ ዞን የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ የድምፅ መስጠት ሂደት ዛሬ ማለዳ 12፡00 የተጀመረ ሲሆን፤ ቦርዱ የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔውን የሚያስፈጽሙ ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በተለያየ መንገድ መልምሎና አሠልጥኖ አሠማርቷል። ከነዚህም ውስጥ ከአዲስ አበባ 5215 የምርጫ አስፈጻሚዎችና 3845 ከወላይታ ዞን የምርጫ አስፈጻሚዎችን አሣትፏል።

በዛሬው ዕለት ሁሉም አስፈፃሚዎች በሥራ ላይ ተሠማርተው መራጮችን በማስተናገድ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በአንድ’ዳንድ ሠልፍ በበዙባቸው ጣቢያዎች ላይ ቦርዱ አሠልጥኖ በተጠባባቂነት የያዛቸውን አስፈጻሚዎችን እንዲሠማሩ አድርጓል። በተጨማሪም ቦርድ በ1812 የምርጫ ጣቢያዎች የተሟላ የምርጫ ቁሳቁሶች መድረሳቸውን አረጋግጧል።

ከጠዋት 12፡00 ሰዓት እስከ ቀኑ 6፡00 ሰዓት በተገኘው መረጃ መሠረት 370,552 መራጭ ድምፅ ሰጥተዋል። በተያያዘም የድምፅ መስጠት ሂደቱን ለመታዘብ ከቦርዱ ዕውቅና ያገኙ ሦስት የሀገር ውስጥ ተቋማት 214 ታዛቢዎችን በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ አሠማርተዋል።

የድምፅ መስጠት ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ በርከት ያሉ መራጮች የያዙት መታወቂያ ከተሠጣቸው ስድስት ወር ያልሞላው ሆኖ የተገኘ ሲሆን፤ ነገር ግን የቦርዱ መመሪያ የሚያዘው አንድ ዜጋ ድምፅ መስጠት የሚችለው ድምፅ በሚሰጥበት አካባቢ ቢያንስ ለስድስት ወር እና ከዚያ በላይ መኖሩ መረጋገጥ ሲችል ነው። በመሆኑም እነዚህ መራጮች ከያዙት የነዋሪነት መታወቂያ በተጨማሪ ነዋሪነታቸውን የሚያረጋግጡበት የሦስት ሰዎች ምሥክርነት ወይም ሌሎች ሕጋዊ የሠነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም