Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በዎላይታ ዞን ለሚያስፈጽመው የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ ምርጫ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ወደ ዎላይታ ዞን የማጓጓዝ ሥራ ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሁለት ቀናት በኋላ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በዎላይታ ዞን ለሚያስፈጽመው የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ ምርጫ የተለያዩ የቅድመ ምርጫ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል። ከነዚህም የቅድመ ምርጫ ተግባራት ውስጥ አንዱ ከአዲስ አበባ በመመልመል ያሠለጠናቸውን የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ከአዲስ አበባ የሕዝበ ውሣኔው ወደ’ሚካሄድበት ዎላይታ ዞን ውስጥ ወደ’ሚገኙ 1,804 ምርጫ ጣቢያዎች በሁለት ዙር ማጓጓዝ ይጠቀሳል። በዚህም ሰኔ 6 እና ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በድምሩ 5215 አስፈጻሚዎች ወደ ዎላይታ ዞን የማጓጓዝ ሥራው ተጠናቋል።

ለምርጫ ቀን አስፈላጊ የሆኑ የምርጫ ቁሳቁስ ሥርጭቱም በትላንትናው ዕለት ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፤ እስከ ምሽት ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በ743 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የቁሳቁስ ሥርጭቱን ማጠናቀቅ ተችሏል። ቦርዱ ቀደም ሲል ለሕዝበ ውሣኔ ምርጫው 1,804 ምርጫ ጣቢያዎች እንዲዘጋጁ ያደረገ ሲሆን፤ የምርጫ ሂደቱን ፍሰት ለማቀላጠፍ በማሰብ ተጨማሪ ስምንት ጣቢያዎች እንዲዘጋጁ አድርጓል፤ በዚህም የምርጫ ጣቢያዎቹን ቁጥር ወደ 1812 ከፍ እንዲሉ ተደርጓል።

Share this post