የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን ለሚያካሄደው የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በወላይታ ዞን የሚያካሄደው የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ ላይ ለሚሣተፉ በየደረጃው ለሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠና ሰጠ። ከግንቦት 16 ቀን እስከ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም በተሰጠው ሥልጠናም የሥራ ትውውቅ፣ የውጤት ማመሳከር፣ የማዳመርና የይፋ አደራረግ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለዞንና ለማዕከል አስተባባሪዎች የተሰጠ ሲሆን፤ ለመሥክ አሠልጣኞችም እንዲሁ የአሠልጣኞች ሥልጠና በሶዶ ከተማ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም ቦርዱ በወላይታ ዞን ውስጥ በተቋቋሙ 12 ማስተባበሪያ ማዕከላት ላይ ለ3608 የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች በሁለት ዙር ሥልጠና በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ዙር ሥልጠና ከግንቦት 23 እስከ ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም ሲሰጥ፤ የሁለተኛ ዙር ሥልጠናም እንዲሁ ከግንቦት 26 እስከ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም የሚሰጥ ይሆናል።
በወላይታ ዞን የተካሄደውን የሕዝበ ውሣኔ ምርጫ ለምን መድገም እንዳስፈለገ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፤ ይኸውም በወላይታ ዞን የተፈጸሙ የሕግ ጥሠቶችን፤ ከድምፅ አሰጣጥና ውጤት አስተዳደር/አገላለጽ ሂደት ጋር የተያያዙ ምርጫ ነክ ወንጀሎችን፣ የሚያስከትሉትን የወንጀል ተጠያቂነትና የምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈጻሚዎች ኃላፊነቶችን የሥነ-ምግባር ደንብ በማጣቀስ ጭምር ሥልጠናው ተሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ ከመራጮች ምዝገባና ድምፅ መስጫ ቀን አስቀድሞ ስለሚደረጉ ዝግጅቶች እንዲሁም የምርጫ ጣቢያዎችን ተደራሽና አካታች ለማድረግ መሠራት ስላለባቸው ሥራዎች፤ በመራጮች ምዝገባና በድምፅ መስጫ ቀንም ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ቁሳቁሶች የተመለከተ ገለጻ በዝርዝር ቀርቧል፡፡
በሥልጠናው ወቅት በመራጭነት የመመዝገብና የድምፅ መስጠት ሂደትን፣ የድምፅ ቆጠራ ሂደትን፣ የውጤት ማመሳከርና መለየትን፤ እንዲሁም የምርጫ ጣቢያ ቁሳቁሶች በሚታሸጉበት ወቅት መከተል ስለሚገባው ሥርዓት በንድፈ ሃሳበና በተግባር ልምምድ የታገዘ ሥልጠና ተሰጥቷል።