የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (በኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጌዴኦ፣ በጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (በቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ በአሌ፣ በአማሮ፣ በዲራሼ) ያካሄደውን የሕዝበ ውሣኔ ውጤት ስለማሳወቅ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (በኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጌዴኦ፣ በጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (በቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ በአሌ፣ በአማሮ፣ በዲራሼ) ላይ ያካሄደውን የሕዝበ ውሣኔ ጊዜያዊ ውጤት የማዳመር ሥራ በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ላይ አጠናቆ በዞንና በልዩ ወረዳ ደረጃ ጊዜያዊ ውጤቶች ይፋ ተደርገዋል።
ቦርዱ የመጨረሻውን ውጤት የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ አርባ ምንጭ ከተማ በሚገኘው የሕዝበ ውሣኔው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እየሰራ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል ቦርዱ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ የመጨረሻውን በቦርድ የተረጋገጠ ውጤት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ይፋ እንደሚያደርግ የገለፀ ቢሆንም በርከት ያሉ ግድፈቶችና የምርጫ ህግ ጥሰቶች በቦርዱ የምርጫ ክትትል ቡድን እንዲሁም በምርጫ ታዛቢዎች ሪፖርት በመቅረቡ የማጣራት እና ውጤት የማረጋገጥ ስራን በታቀደበት ግዜ ለማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡
በዚህም የውጤት ማጣራትና ማረጋገጥ ስራ የዲራሼ፣ አሌ፣ ደቡብ ኦሞ፣ባስኬቶ፣ ኮንሶ እና ቡርጂ ውጤቶችን የማጣራትና የማረጋገጥ ስራ ተጠናቆ ውጤታቸው በቦርዱ ፀድቋል። በቀጣይም በቀሪዎቹ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ማለትም በአማሮ፣ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጌዴኦ እና የጎፋ ግዜያዊ ውጤቶች የማጣራትና የማረጋገጥ ሂደት እንደተጠናቀቀ ቦርዱ ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
በቦርዱ ታይቶ የፀደቀውን ውጤት ለማግኘት እዚህ ላይ ይጫኑ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ