የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (በኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጌዴኦ፣ በጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (በቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ በአሌ፣ በአማሮ፣ በዲራሼ) ላይ ያካሄደውን የሕዝበ ውሣኔ ጊዜያዊ ውጤት የማመሳከር ሥራ በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ላይ አጠናቆ በዞንና በልዩ ወረዳ ደረጃ ጊዜያዊ ውጤቶችን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

ቦርዱ የመጨረሻውን ውጤት የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም አርባ ምንጭ ከተማ በሚገኘው የሕዝበ ውሣኔው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የጀመረ ሲሆን፤ ይህንን የመጨረሻ የሆነውን የውጤት ማጣራትና ማረጋገጥ ሥራ ለመታዘብ በቦርዱ ዕውቅና የተሰጣችሁ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች እና በቦርዱ የዘገባ ፍቃድ የተሰጣችሁ የመገናኛ ብዙኃን አካላት እንዲሁም ቦርዱ በድጋሚ ያካሄደውን የቡሌ ምርጫ ውጤት የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራ ለመታዘብ ዕውቅና የተሰጣችሁ የፓርቲ ወኪሎች በሙሉ በማስተባበሪያ ማዕከሉ በመገኘት የውጤት ማጣራትና ማረጋገጥ ሂደቱን መታዘብ የምትችሉ መሆኑን ቦርዱ ያሳውቃል።

በቀጣይም ቦርዱ በማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የተጣራውንና በቦርዱ የተረጋገጠውን የመጨረሻው የሕዝበ ውሣኔ ውጤት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

 

ማስታወቂያ
የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም.