የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሣኔ የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ላይ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሣኔ የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።
የቦርዱ የሎጅስቲክ ሥራ ክፍል ለሕዝበ ዉሣኔው ድምፅ መስጫ ቀን የሚያገለግሉ የተለያዩ ሠነዶችና ቁሳቁሶችን (መጠባበቂያን ጨምሮ) ለ3,769 ምርጫ ጣቢያዎች ለሥርጭት ዝግጁ በሆነ መልኩ የማሸግ ሥራውን አጠናቋል። በእሽጉ ውስጥ ከተካተቱ ሠነዶች እና ቁሳቁሶች መካከል የድምፅ መስጫ ወረቀቶች፣ የሕዝበ ዉሣኔው ውጤት ማመሳከሪያ እና ማሳወቂያ እንዲሁም በድምፅ መስጫ ቀን ጥቅም ላይ የሚውሉ ሌሎች አስፈላጊ ሠነዶች ይገኙበታል።
በቀጣይም ቦርዱ ከላይ የተጠቀሱትን ሠነዶችና ቁሳቁሶች ወደ’ተመረጡ የሕዝበ ዉሣኔው ማስተባበርያ ማዕከላት የሚያሠራጨ ሲሆን፤ በተዋረድም ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የሚያሠራጭ ይሆናል።