የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ (ኢ. ነ. ፓ) ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ በሚመለከት ቦርዱ ያሳለፈዉ ዉሳኔ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ (ኢ. ነ. ፓ) ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ በሚመለከት ፓርቲው ከሪፖርት ጋር አያይዞ ያቀረባቸውን ሠነዶች ከሕጉ፣ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ እና የቦርዱ ታዛቢዎች ካቀረቡት ሪፖርት አንጻር መርምሮ ውሣኔ አሣልፏል።
ቦርዱ ባደረገው ምርመራ ፓርቲው ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የፓርቲ አባላት ያልሆኑ በልመና ተግባር የተሠማሩ በአበል ክፍያ በጉባዔው ላይ እንዲሣተፉ ማድረጉንና የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ለጉባዔው ቀርቦ ሳይፀድቅ ፓርቲው ደንቡ ቀርቦ እንደፀደቀ በማስመሰል ለቦርዱ የሰጠውን የተሣሣተ መረጃ መሠረት በማድረግ ፓርቲው ከሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ መታገዱን በመግለጽ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 98/3/ መሠረት መከላከያውን እንዲያቀርብ ቦርዱ በሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. በቁጥር አ1162/11/641 በተጻፈ ደብዳቤ ለፓርቲው አሳውቋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ፓርቲው በሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በጽሑፍ ያቀረበው መከራከሪያ አሳማኝ ባለመሆኑ ቦርዱ አልተቀበለውም።
በዐዋጁ አንቀጽ 98/1(ሠ)/ የፖለቲካ ፓርቲው በማጭበርበር ወይም ዕያወቀ ወይም ማወቅ የተገባው ሆኖ ሳለ አሣሣች መረጃ በማቅረብ የተመዘገበ ከሆነ ወይም በዐዋጁ መሠረት መረጃ ሲጠየቅ የሐሰት መረጃ ለቦርዱ የሰጠ እንደሆነ ቦርዱ ፓርቲውን ከምዝገባ ሊሠርዝ እንደሚችል በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት ቦርዱ ፓርቲው በፈጸማቸው ጥፋቶች ምክንያት ከምዝገባ እንዲሠረዝ መወሠኑን ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።