Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታኅሣሥ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ለመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መ. ኢ. አ. ድ) ሚያዚያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ በሚመለከት ቦርዱ ያሳለፈዉ ዉሳኔ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታኅሣሥ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መ. ኢ. አ. ድ) ሚያዚያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ በሚመለከት ፓርቲው ከሪፖርት ጋር አያይዞ ያቀረባቸውን ሠነዶች ከሕጉ፣ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ እና የቦርዱ ታዛቢዎች ካቀረቡት ሪፖርት አንጻር መርምሮ ውሣኔ አሣልፏል።

ቦርዱ ባደረገው ምርመራ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የተካሄደው የፓርቲው የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ አባላት፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እና የተጓደሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እጅ በማውጣት መደረጉ በዐዋጅ አንቀጽ 74(3) መሠረት በየደረጃው ያሉ አመራሮች አመራረጥ ግልጽ፣ ነፃ እና ፍትሐዊ እንዲሁም በሚሥጥር በሚሰጥ ድምፅ የሚመረጡ መሆን እንዳለበት ከሚደነግገው ጋር የተቃረነ በመሆኑ ፓርቲው ሕጉን መሠረት በማድረግ በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ ሊያካሂድ እንደሚገባ ወሥኗል።

በተጨማሪም በተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ በዐዋጁ መሠረት ተሻሽለው መቅረብ ያለባቸውን አንቀጾች ቦርዱ የለየ ሲሆን፤ በዚም አግባብ ከሕጉ ጋር የሚቃረኑ የደንቡ አንቀጾች የታገዱና በዐዋጅ 1162/2011 ላይ በዝርዝር የሠፈሩት ድንጋጌዎች በተግባር እንዲፈጸሙ እንዲደረግ፤ እንዲሁም ይህ ውሣኔ ከተገለጸበት ከታኅሣሥ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ማለትም እስከ ሚያዚያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያካሂድ፤ ይህም ሲሆን በድጋሜ የሚደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ሕጉንና የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች በተከተለ መልኩ መሆን እንዳለበት ቦርዱ ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።

የውሣኔውን ሙሉ ዝርዝር ደብዳቤ እዚህ ላይ ያገኙታል

Share this post