የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ የሚያካሂደውን ሕዝበ ውሣኔ ለመዘገብ ከቦርዱ ዕውቅና ላገኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ላይ የሚያካሄደውን ሕዝበ ውሣኔ ለመዘገብ አመልክተው ከቦርዱ ዕውቅና ለተሰጣቸው የመገናኛ ብዙኃን ባሙያዎች ታኅሣሥ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. የተሰጠውን ሥልጠና በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ እንደ አዲስ ከተቋቋመ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚደረገው ሕዝበ ውሣኔ ሦስተኛው እንደሆነ አስታውሰው፤ መገናኛ ብዙኃኑ በሕዝበ ውሣኔው ሂደት በሚሠሯቸው ዘገባዎች ከወገንተኝነትና ከጥቅም ግጭት ነፃ ሆነው ኃቅንና ሙያዊ ሥነ-ምግባርን መሠረት ባደረገ መልኩ መዘገብ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።
ምርጫ በኢትዮጵያ፣ የምርጫ ዓይነቶች እና ባህሪያት፣ የምርጫ ዑደት፣ የመገናኛ ብዙኃን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነ-ምግባር እና አሠራር መመሪያ ላይ የተቀመጡ የመገናኛ ብዙኃኑ መብትና ግዴታዎችን እንዲሁም ኃቅን ማጣራት፣ የሐሰተኛና የአደናጋሪ ዜናዎች ልዩ ባህሪያት፣ የተዛባ መረጃን የመለያ መንገዶች በሥልጠናው ትኩረት ከተደረገባቸው ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ቦርዱ ሕዝበ ውሣኔውን ለመዘገብ ፍላጎት ላላቸው መገናኛ ብዙኃን ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ከሬዲዮ፣ ከቴሌቭዥን፣ ከኅትመትና ከኦንላየን የተውጣጡ 17 መገናኛ ብዙኃን አመልክተው፤ ለ171 ዘጋቢዎቻቸው የዕውቅና ባጅ አግኝተዋል።