የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በታዛቢነት የመሣተፍ ፍላጎት ላላቸው የሀገር በቀል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥልጠና እና ዕውቅና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ዎላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ላይ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚካሄደው ሕዝበ ውሣኔ በታዛቢነት የመሣተፍ ፍላጎት ላላቸው የሀገር በቀል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወቃል።
በዚህም መሠረት ስድስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማመልከቻቸውን አስገብተው የተገመገሙ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ አራቱ ግምገማውን አልፈውና አስፈላጊውን ሥልጠና ወስደው ዕውቅና አግኝተዋል። ዕውቅና ያገኙት ታዛቢ ድርጅቶች ባመለከቱት መሠረት ለጠቅላላው የምርጫ ዑደት 5,274 ታዛቢዎችን እንደሚያሰማሩ ይጠበቃል።
ግምገማውን ያለፉት ታዛቢ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች
• የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ (CECOE)፣
• ድሬ የተቀናጀ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት (DICDO)፣
• የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ/EHRCO) እና
• የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ናቸው።
በሕዝበ ውሣኔው የመራጮች ምዝገባ ሂደት፤ ኢ.ሰ.መ. ኮ’ን ጨምሮ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ 117 ታዛቢዎችና 17 ሰብዓዊ መብት ተቆጣጣሪዎች በመሥክ ላይ ይገኛሉ።