የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢ.ሰ.መ.ኮ) የሰብአዊ መብት ተከታታዮች እውቅና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ዎላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ላይ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ እና በቡሌ ምርጫ ክልል የሚፈፀመው የድጋሚ ምርጫ ሂደት የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ እንዲከታተሉ ለ 17 የኢ.ሰ.መ.ኮ ሰራተኞች የሰብአዊ መብት ተከታታይነት (Human Rights Monitors) እውቅና ሰጠ።
የሰብአዊ መብት ተከታታዮቹ በምርጫ ጣቢያዎች እና የምርጫ ማስተባበሪያ ፅ/ቤቶች ተገኝተው ለኮሚሽኑ በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብት ክትትልን አስመልክቶ በህግ የተሰጠውን ሀላፊነት በአስቻይ ሁኔታ ለመፈፀም የሚያስችል የመለያ ካርድ ወይም ባጅ በቦርዱ የተሰጣቸው ፣ የምርጫ ህጉን እና ኮሚሽንኑ ያቋቋመውን አዋጅ-ማእቀፍ በማድረግ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መካከል ታህሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ መሰረት በማድረግ ነው።
የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብት ክትትል የመራጮች ምዝገባ ወቅት፣ በህዝበ ውሳኔ ድምፅ መስጫ እለት እና የድህረ ህዝበ ውሳኔ ምርጫ ወቅትንም ይጨምራል።ኮሚሽኑ የመራጮች ምዝገባ ክትትሉ በአምስት ዞኖች በአንድ ልዩ ወረዳ እና ተፈናቃይ ዜጎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የተለያዩ መመዘኛዎችን በመጠቀም የክትትል ቦታዎችን በመምረጥ እንዲሁም የተለያዩ ስነ-ዘዴዎችን በመጠቀም ክትትሉን እንደሚያካሂድ ለቦርዱ ገልጿል ።