የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በደብረ-ብርሃን ከተማ ያካሄደውን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ አስመልክቶ ታህሳስ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የተሰጠዉ የዉሳኔ ደብዳቤ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በደብረ-ብርሃን ከተማ ያካሄደውን 2ኛ መደበኛ ጉባዔና ውጤቱን ከሕጉና ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንጻር መርምሮ ሕጉን ያልተከተሉ ውሣኔዎች በማግኘቱ ያላጸደቀ መሆኑን ገልጾ፤ ቦርዱ ዕውቅና የሚሰጠው ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. የፀደቀውን የፓርቲውን ሕገ-ደንብ፤ ብሔራዊ ምክር ቤት እና ሌሎች የፓርቲው አካላትን ብቻ እንደሆነ ማሳወቁን ተከትሎ፤ ፓርቲው የቦርዱ ውሣኔ አግባብነት እንደሌለው ገልጾ ሥራ አመራር ቦርዱ ጉዳዩን መርምሮ የዕርምት ውሣኔ እንዲሰጥልን ሲል ታኅሣሥ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ለቦርዱ በላከው ደብዳቤ አመልክቷል፡፡
ምንም እንኳን ቦርዱ ፓርቲው የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ያካሄደው ጉባዔ በሕጉ የተቀመጠውን መሥፈርት ባለማሟላቱ እንዳልተቀበለው ለፓርቲው ገልጾለት የነበረ ቢሆንም፤ ፓርቲው የተጓደሉ የተባሉ ነጥቦችን አሟልቶ ጉባዔ እንዲያደርግ ቦርዱ በመስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም እና በሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሳወቀው መሠረት ተከታትሎ መመሪያውን ለማስፈጸም፤ ሰኔ 2013 ዓ.ም እና መስከረም 2014 ዓ.ም ለተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ቦርዱ የተለያዩ ክንዋኔዎችን ሲመራና ውሣኔዎችን ሲያስተላልፍ የቆየበትና ከፍተኛ የሥራ ጫና ያስተናገደበት ጊዜ በመሆኑ አስቻይ ሁኔታዎች አልነበሩም። ይህም ምክንያት ሆኖ ፓርቲው በደብረ-ብርሃን ያደረገው ጉባዔ ውጤት የሆኑት የፓርቲው ደንብ እና በጉባዔው የተመረጡ አመራር አካላት ሥራቸውን በመቀጠል ከቦርዱ ጋር የሚያገናኛቸውን ተግባራት በሙሉ ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
ቦርዱ ከላይ የተጠቀሱትን ሁነቶች በጥልቅ በመመልከት፤ አሁን በሥራ ላይ ያሉትና በደብረ-ብርሃኑ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡት የፓርቲው አመራር አካላትን ዕውቅና አለመስጠት ፓርቲው ለሦስት ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራት ዋጋ አልባ የሚያደርግ መሆኑን ከመገንዘቡም በላይ፤ የፓርቲውን ኅልውና ለማስቀጠል ሲባል፤ ቦርዱ በታኅሣሥ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ለፓርቲው የጻፈው ደብዳቤ ላይ ማስተካከያ በማድረግ፤ የደብረ-ብርሃኑ ጉባዔና ያስተላለፋቸውን ውሣኔዎችም ሆኑ የውሣኔዎቹን ውጤቶች ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል ሲል ቦርዱ የማስተካከያ ውሣኔ ሰጥቷል። ይህም ሲሆን ፓርቲው በቀጣይ ሊጠራው በሚገባው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ሊከተላቸው የሚገቡ ዝርዝር ሁኔታዎችን ቦርዱ ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።