የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ለአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አሰመልክቶ ታህሣሥ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. የተሰጠዉ ምላሽ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ታኅሣሥ 3 እና 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቦርዱ በተጻፉ ደብዳቤዎች 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማድረግ የሚያስችሉትን የቅድመ ጉባዔ ሥራዎች ማጠናቀቁን ገልጾ፤ ጉባዔውን ታኅሣሥ 22 እና 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ መወሠኑን አሳውቋል።
ቦርዱም የቀረበውን ጥያቄ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንጻር የመረመረ ሲሆን፤ በደንቡም ላይ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት መደበኛ፣ ልዩ እና አስቸኳይ ስብሰባዎችን የመጥራት እንዲሁም የጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴም የማቋቋም ሥልጣን ያለው መሆኑን ተመልክቷል። ሆኖም ግን ፓርቲው ከላይ በተጠቀሱት ቀናት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማድረግ ያሳለፈው ውሣኔ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በሚያዘው መሠረት የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ምልዓተ ጉባዔ ባልተሟላበት ሁኔታ መሆኑን ቦርዱ ፓርቲው ከላከው ሠነድ ማረጋገጥ ችሏል፤ ስለዚህም ምልዓተ ጉባዔው ባልተሟላበት ሁኔታ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ውሣኔ መሠረት ይህን ጠቅላላ ጉባዔ መጥራትና ማካሄድ የሚቻልበት የሕግ አግባብ የሌለ መሆኑን ቦርዱ ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።