የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኅዳር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል ጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ፓርቲውን ወክለው በ6ኛው ሀገር ዐቀፍ ምርጫ ተወዳድረው የክልል ምክር ቤት አባል የሆኑትን አባሉ ኅዳር 17 ቀን 2015 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን፤ ኅዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ደ’ሞ በተያዙበት ወቅት አካላዊ ጉዳት ስለደረሰባቸው የሕክምና ዕርዳታ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች በመጠየቅ ለቦርዱ አቤቱታ ማቅረቡን ተከትሎ፤ ቦርዱም በዐዋጁ በተጣለበት ኃላፊነት መሠረት ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲሰጠው አሳውቋል።

ይሁንና ፖሊስ ኮሚሽኑ ይህ ደብዳቤ እስከ’ተጻፈበት ቀን ድረስ ለቦርዱ ጥያቄ ምላሽ ባለመስጠቱ፤ ቦርዱ ለሦስተኛ ጊዜ ደብዳቤ ለመጻፍ ተገዷል። በመሆኑም የምርጫ ዐዋጁ አንቀጽ 161 ማንኛውም ሰው ዐዋጁን በሥራ ላይ ለማዋል በሚያስችል ሁኔታ የመተባበር ግዴታን ይጥላል፡፡ ሰለዚህ ኮሚሽኑ ይህንን የሕግ ግዴታ በመረዳት ከላይ በኮሚሽኑ ላይ በኢዜማ ፓርቲ የቀረቡትን አቤቱታዎች በተመለከተ አጣርቶ ምላሽ ያልሰጠበትን ምክንያት እንዲገልጽ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የደረሰበትን ሂደት በአስቸኳይ እንዲያሳውቅ ቦርዱ ለፖሊስ ኮሚሽኑ በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።

ደብዳቤው እዚህ ላይ ያገኙታል

ታህሣሥ 7 ቀን 2015 ዓ.ም.