የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲ.አ.ን) ፓርቲን እስክ ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያደርግ ማሳወቁን ተከትሎ 32 የሚሆኑ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተሰብስበው ባሳለፉት ውሣኔ፤ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ለመጥራት ሊቀ-መንበሩ ወይም ምክትል ሊቀ-መንበሩ ከሌሉ ዋና ጸሐፊው በጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቅራቢነት በሥራ አስፈጻሚ አፀድቆ ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት እንዲችል የወሠኑትን ውሣኔ ለቦርዱ አሳውቀዋል። በሌላ በኩል 51 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከአባልነት መሠረዛቸውንም እንዱሁ አቅርበዋል። ሆኖም ግን ቦርዱ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ውሣኔዎች ከዐዋጁና ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንጻር በመመርመር ፓርቲው አሳለፍኩት ያለው ውሣኔ ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጪ ምልዓተ ጉባዔው ባልተሟላበት የተሰጠ በመሆኑ፤ ተሠረዙ የተባሉት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ላይ የተላለፈውም ውሣኔ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የተላለፈ ስለመሆኑ፤ እንዲሁም ይህ ውሣኔ በፓርቲው የተላለፈበትን ሂደት የሚያሳይ አንዳችም ማስረጃ ያልቀረበ በመሆኑ ቦርዱ ውሣኔዎቹን ውድቅ አድርጓል።

በመጨረሻም ቦርዱ ፓርቲው እስክ ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያደርግ በሰጠው ውሣኔ መሠረት ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔውን አላደረገም። ስለሆነም ፓርቲው በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ በማቋቋም እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችን ሁሉ በመፈጸም ይህ ውሣኔ ከተገለጸበት ከኅዳር 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ ማለትም እስከ ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ጉባዔውን እንዲያካሂድ ሲል መወሠኑን ቦርዱ ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡

ደብዳቤው እዚህ ላይ ያገኙታል

ኅዳር 17 ቀን 2015 ዓ.ም.