የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ እነአቶ ዘለሌ ጸጋሥላሴ (19 ሰዎች) ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን አስመልክቶ ያቀረቡትን የተለያዩ ቅሬታዎች ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ መርምሯል። በዚህም መሠረት የሁሉም የፓርቲው አባላት አቤቱታዎች ዋና መነሻ የፓርቲው ደንብ ድንጋጌዎች ተጥሰዋል የሚል ነው። ይህንን ዓይነት አቤቱታዎች በፓርቲው አባላት ሲቀርቡ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 15.2.2፤ 15.2.4፤ 24 እና ተከታዮቹ መሠረት በቅድሚያ በፓርቲው የቅሬታ አፈታት ሥነ-ሥርዓት መሠረት ለሚመለከተው የፓርቲው የውስጥ አደረጃጀት መቅረብ ያለበት በመሆኑ፣ ቅሬታ አቅራቢዎች በቅድሚያ ይህንን ሂደት ተከትለው ቅሬታቸውን ለፓርቲው ለሚመለከተው አካል አቅርበው ዕልባት ማግኘት አለማግኘታቸውን (ጥረት ማድረጋቸውን) ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የፓርቲን የውስጥ አለመግባባት ቦርዱ እንዲያየው ሊቀርብ አይገባም ሲል መወሠኑን ቦርዱ ለቅሬታ አቅራቢዎቹ በላከው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡
ኅዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም.