የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ለሚሠማሩ አስተባባሪዎቹ ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ በሕዝበ ውሣኔው የዞን/ልዩ ወረዳ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች እና ማስተባበሪያ ማእከላት ለሚሠማሩ አስተባባሪዎቹ ኅዳር 21 እና 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በሁለት ዙር ሥልጠና ሰጠ።
የሕዝበ ውሳኔውን አደረጃጀትና አፈጻጸምን የተመለከቱ ተግባራት ላይ የተሰጠውን ሥልጠና የወሰዱት 37 የሕዝበ ውሣኔው ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሠራተኞችና 136 የሕዝበ ውሣኔው ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪዎች ሲሆኑ በሥልጠናውም ሕዝበ ውሳኔውን የተመለከተ መሠረታዊ ማብራሪያ፣ የቅጥር ሁኔታን፣ የሥራ ሂደቱ ፍሰት ቅደም ተከተልን፣ የክፍያ እና አስፈላጊ የቢሮ ቁሳቁሶች ርክክብን፣ በየደረጃው የሚገኙ የሕዝበ ውሳኔው ጽ/ቤቶች አደረጃጀትን፣ ከምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ሥልጠና ጋር የተያያዙ ተግባራትን፣ የሕዝበ ውሳኔው ሠነዶችና ቁሳቁስ ሥርጭትን እና የርክክብ ሂደትን አስመልክቶ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓል።
በተጨማሪም ቦርዱ በቅርቡ ቅጥር ለፈጸመላቸው ጀማሪ ባለሙያዎች እና አዲስ ተመራቂዎች ፤ በቦርዱ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ተሠማርተው በቀላሉ ልምድ እየወሰዱ በተመሳሳይ ሁኔታ የሥራ ክፍሎቹ ሕዝበ ውሳኔውን አስመልክቶ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ ድጋፍ መስጠት የሚያስችሏቸውን መሠረታዊ ሥልጠናዎች ሰጥቷል። በሥልጠናውም የዜጎች የመምረጥ መብትን፣ ስለምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ድንጋጌዎች፣ ስለዓለም ዐቀፍ የምርጫ መርኆች፣ እንዲሁም ምርጫ ነክ ተግባራትን በተመለከተ ዝርዝር ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
በጊዜያዊነት ተመድበው በሚሠሩባቸው የሥራ ክፍል ኃላፊዎች አማካኝነትም የሥራ ክፍሎቹን የሥራ ተግባራት የተመለከተ ማብራሪያ እና ሠልጣኞቹ በሕዝበ ዉሣኔው ስለሚኖራቸዉ ሚና ገለጻ ተደርጎላቸዋል። ሠልጣኞቹ በቦርዱ የሎጂስቲክስ፣ የሲቪክና የመራጮች ትምህርት፣ የኮሚኒኬሽንና የውጭ ግንኙነት እንዲሁም የሥርዓት ፆታ እና አካታችነት የሥራ ክፍሎች ውስጥ የሚሠማሩ ይሆናል።