Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥርዓተ ፆታ አካታችነትን አስመልክቶ ለቦርዱ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች እና ባለሞያዎች ሥልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥቅምት 21 እና 22 ቀን 2015 ዓ.ም. የቦርዱን ተግባራት የሥርዓተ ፆታ እና አካታችነትን ባማከለ መልኩ እንዲፈጸም የሚያስችል ሥልጠና ሰጠ። ይህ የቦርዱን የሥራ ክፍል ኃላፊዎች እንዲሁም ባለሞያዎች ዐቅም ለመገንባት ታስበው በመሰጠት ላይ ካሉት ሥልጠናዎች መካከል አንዱ የሆነው ሥልጠና ዐላማው፤ የተሣታፊዎችን የሥርዓተ ፆታ ግንዛቤ ከማሳደግም ባለፈ በፖሊሲ ቀረጻ እንዲሁም በዕቅድ አወጣጥ እና አተገባበር ላይ ታሳቢ መደረግ ስለሚኖርባቸው የሥርዓተ ፆታና አካታችነት አሠራሮች ተለይተው እንዲታወቁ ማድረግ ሲሆን፤ በተጨማሪም የሥራ ክፍሎቹን የዕለት ተለት ሥራዎቻቸውን እንዴት ሥርዓተ ፆታና አካታችነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መፈጸም እንዳለባቸው ክኅሎት ማስጨበጥ ነው።

ሥልጠናውን የቦርዱ የሥርዓተ ፆታ እና ማኅበራዊ አካታችነት የሥራ ክፍል ከUN Women ጋር በመተባበር የሰጠው ሲሆን፤ በቀጣይም ለቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ባለሞያዎች የሚሰጥ ይሆናል።

በዚህ የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ላይ ለተሣተፉ ሠልጣኞች የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳ የተሣትፎ የምሥክር ወረቀት ሰጥተዋል።

Share this post