Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል የሚካሄደውን ሕዝበ ውሣኔ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥቅምት 1 እና 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ የጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዲዮ፣ኮንሶና፣ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣አማሮ፣ደራሼ፣ባስኬቶ፣አሌ ልዩ ወረዳዎች የሚካሄደውን ሕዝበ ውሣኔ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄዷል። የመድረኩ ዐላማ የሕዝበ ውሣኔው አጠቃላይ ዕቅድና የዝግጅት መለኪያዎች፣ የሕዝበ ውሣኔው አደረጃጀት፣ እያንዳንዱን የታቀዱ ተግባራት ለመፈጸም የሚያስፈልገው የጊዜ ሁኔታ፣ ከአስተዳደር አካላትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ ኃላፊነቶችን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከርና ተጨማሪ ግብዓት በመውሰድ የመጨረሻውን የጊዜ ሠሌዳ ማዘጋጀት እንደሆነ ተጠቅሷል ፡፡

በምክክር መድረኩ የሕዝበ ውሣኔ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳና የሕዝበ ውሣኔው አፈጻጸም ዝርዝር ዕቅዶች በሁለት ተከታታይ ቀናት ለተሣታፊ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና እንዲሁም ለመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች የቀረበ ሲሆን፤ ለሕዝበ ውሣኔው 541,270,104.82 ብር በጀት እንደሚያስፈልገው፤ ቦርዱ ሕዝበ ውሣኔን የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶም ፀጥታ ሁኔታውን የሚከታተል ቡድን የሚያደራጅ መሆኑም ተገልጿል።

በምክክሩ የተሣተፉ የፓርቲ ወኪሎች፤ በየምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኝነትን፣ የሕዝብ ድምፅ መከበርን፣ በገዢው ፓርቲ ሊደርስ የሚችል ተፅዕኖን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ የፀጥታ ችግሮችን፣ የጌዴኦ ዞን በሕዝበ ውሣኔ መካተትን እንዲሁም የሕዝበ ውሣኔውን አጠቃላይ ፋይዳን የሚመለከቱ አስተያየትና ጥያቄዎችን አቅርበው በቦርዱ አመራሮች እና ባለሞያዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች ጋር በተደረገው ምክክርም፤ በቦርዱ የኦፕሬሽን የሥራ ክፍል ባልደረቦች አማካኝነት የሕዝብ ውሣኔው አጠቃላይ ዕቅድና አፈጻጸሙን የተመለከተ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፤ በቦርዱ የሥርዓተ ፆታና አካታችነት ሥራ ክፍል እንዲሁም በኮሚኒኬሽን ሥራ ክፍል ባልደረቦች አማካኝነት ከሁለቱም ባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል የሚለውን የሕዝበ ውሣኔውን ስኬታማነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ምክክር ተደርጓል።

በሂደቱ በዋናነት የመዘገብ ፍቃድ ጥያቄ አቀራረብ እና አሰጣጥ፣ ስለዕውቅና ጥያቄ አቀራረብ እና አሰጣጥ፣ ከጥያቄው ጋር ተያይዞ ስለሚቀርብ ሠነድ የምርጫ ሂደትን ለመከታተል ዕውቅና የተሰጠው ጋዜጠኛ መብቶች፣ ግዴታዎች እና ኃላፊነቶች፣ የመራጮች ትምህርት የመስጠት ኃላፊነት፣ የመራጮች ትምህርት የማስተማር ፍቃድ፣ የመራጮች ትምህርት በሕዝበ ውሣኔው ሴቶች ከወንዶች ዕኩል በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠ መብት ያላቸው መሆኑ፣ የመራጮች ትምህርት አሰጣጥ ላይ መከተል ስለሚኖረው ሥነ ምግባር እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሕዝበ ውሣኔውን የመታዘብ መብትና ኃላፊነት ተዘርዝሯል።

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የሕዝበ ውሣኔው ፋይዳ ከሕጋዊነት፣ ሕገ መንግሥታዊነትና ከዴሞክራሲያዊነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ እና ተቋማዊ ኃላፊነቱንም ለመወጣት እና የሕዝብ ፍላጎት ለማወቅ የሚከናወነውን ምርጫ ለማስፈጸም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። በምክክር መድረኮቹ ላይ ተገኝተው ሃሳባቸውን ላጋሩት ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ከፍተኛ ምስጋና ያቀረቡ ዋና ሰብሳቢዋ፤ ነገር ግን ለምክክር የተጋበዙ ሕዝበ ውሣኔው የሚደረግባቸው አካባቢዎች የአስተዳደር ኃላፊዎች በስብሰባው ላይ ሁሉም ሳይገኙ መቅረታቸውን ገልጸው፤ ይህ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ሕዝበ ውሣኔውን በታቀደው ጊዜ መሠረት በመከናወኑ ላይ ጥላ እንደሚያጠላ፤ በሕግ የተቀመጠውን የማንኛውም ተቋም ለምርጫ ሥራ የመተባበር ግዴታንም እንደሚጥስ ገልፀው ለወደፊቱ እንዲታረም አስገንዝበዋል።

Share this post