Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኬንያ የምርጫ ኮሚሽን (Independent Electoral and Boundaries Commission (IEBC)) እና ከኬንያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሬጂስትራር ቢሮ (Office of the Registrar of Political Parties) አመራሮች ጋር የልምድ ልውውጥ አደረገ

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እና በምክትል ሰብሳቢው ውብሸት አየለ የተመራ ልዑክ ከኬንያ የምርጫ ኮሚሽን እና ከኬንያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሬጂስትራር ቢሮ አመራሮች ጋር የልምድ ልውውጥ አደረገ። በልምድ ልውውጥ ላይ የቦርዱ የኦፕሬሽን፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች እና በተለያዩ ኃላፊነት የሚሠሩ የቦርዱ ባልደረቦች እየተሣተፉ ይገኛሉ።

በዚህ የሁለትዮሽ የልምድ ልውውጥ ላይ ከዋነኛ የምርጫ ሂደቶች ውስጥ ከሚካተቱት፤ እንደ የምርጫ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመራጮች ምዝገባ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ፣ እንዲሁም የአስተዳደር እና የፋይናንስ ጉዳዮችን የተመለከቱ አሠራሮችን እና ልምዶችን ለመለዋወጥ ተችሏል።

ምርጫ ቦርድ የልምድ ልውውጡ አካል የሆነውን ውይይት የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ ዋፉላ ዋንዮኒ ቼቡካቲ፣ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮችና ዋና ጸሐፊዎች እንዲሁም የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካፍሏል። በዚህም የልምድ ልውውጥ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ስኬታማ የምርጫ ፕሮግራሞችን የተመለከቱ መልካም ተሞክሮዎችን ከኮሚሽኑ መውሰድ ተችሏል።

በተጨማሪም ከኬንያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሬጂስትራር ቢሮ ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በውይይቱ ላይም ዋና ሬጅስትራል የሆኑት ፍሎረንስ ቢርያ እና የሬጂስትራሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሣትፈውበታል። ውይይቱ እና የልምድ ልውውጡ በቀጣዮቹ ቀናትም የሚቀጥል ይሆናል።

Share this post