Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን አስመልክቶ እያስጠና ያለው ጥናት ላይ ውይይት አካሄደ

መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የባለድርሻ አካላትን ምክረ-ሃሳብ ለመሰብሰብ ታስቦ የተዘጋጀውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ ሲሆኑ፤ በንግግርቸውም ጥናቱን ያከናወኑትን ባለሞያዎችንና የመድረኩ ተሣታፊዎች አመስግነው፤ ከመድረኩ የሚገኙት አስተያየቶች ጥናቱን በተሻለ ለማዳበር ወሣኝ ከመሆኑም ባሻገር ቦርዱ በቀጣይ ለሚያካሂዳቸው ምርጫዎች ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ገልጸዋል። አክለውም ጥናቱ በምርጫ ቦርድ ታሪክ ምናልባትም በዓይነቱ የመጀመሪያ ሊባል የሚችል ነው ብለዋል።

የአመራሯን ንግግር ተከትሎ በጥናት ሂደቱ ተሣታፊ በነበሩትና የዘርፉ ባለሞያ በሆኑት በመሠረት ለገሠ እና ሸዋዬ ሉሉ አማካኝነት ጥናቱ ለተሣታፊዎቹ ቀርቧል። ጥናቱ ሴቶች በምርጫ ላይ ያለቸውን ተሣትፎ ከፍ ለማድረግ ታስቦ እንደተዘጋጀ የገለጹት ባለሞያዎቹ፤ ይህውም በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ዓይነተኛ ባህሪ ከማጥናት ባሻገር ከችግሩ መወጫ ይሆናል ያሏቸውን መንገዶች የሚያሳይ ምክረ ሃሳም እንደተካተተበት ተናግረዋል። በዚህም መሠረት ጥናቱ አጠቃላይ የሴቶችን የምርጫ ተሣትፎ ምን እደሚመስል፣ በምርጫ ሂደት ውስጥ ያሉ የፆታዊ ጥቃት ዓይነት፣ ምክንያታቸውንና ውጤታቸውን ለማየት ተሞክሯል።

በተጨማሪም በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን አስመልክቶ ያሉ የሕግና ማዕቀፎችና ፖሊሲዎች የተዳሰሱ ሲሆን፤ ችግሩን ለማስቀረት ሊወሰዱ የሚገባቸው የአጭር እና የረጅም ጊዜ ርምጃዎች ምን ሊሆኑ እንደሚገባም በዝርዝር ተቀምጧል።

ባለሞያዎቹ ባቀረቡት ጥናት ላይ የውይይቱ ተሣታፊ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የጋራ ምክር ቤት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከተወካዮች ምክር ቤት፣ ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዩች አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል። ይህውም ጥናቱ የተከተለው የመረጃ አወሳሰድ መንገድ ምን እንደሚመስል፣ ጥናቱን እንደተደረገባቸው አካባቢዎች የባህልና የግንዛቤ ተለዋዋጭነት ጥናቱ የሚከተለውን የመረጃ አወሳሰድና መለኪያዎቹን እያስማሙ ለመሄድ የተደረገ ጥረት ካለ፣ ጥናቱ ታሪካዊ ዳራዎችን ቢያካትት፣ የሴት አካል ጉዳተኞች ጥቃት ድርብ ጥቃት እንደመሆኑ መጠን ተነጥሎ በጥናቱ ቢታይ፣ ጥቃቱ በወንዶች እንደመፈጸሙ መጠን በመፍትሔ መፈለጉ ሂደትም በዕኩል ደረጃ እነሱንም አሣታፊ ቢያደርግ፣ መረጃዎቹ በሚሰበሰቡበትና ይፋ በሚደረግበት ሂደት የተጎጂዎቹን ሚሥጥር በመጠበቅ ደረጃ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊወሰድ እንደሚገባ በአስተያየት ሰጪዎቹ አስተያየት ተሰጥቶበታል።

የቦርዱ የሥርዓተ ፆታ እና ማኅበራዊ አካታችነት ክፍል ኃላፊዋ እንዲሁም ጥናቱን ያካሄዱት ባለሞያዎች ከተሣታፊዎች የተሰነዘሩት አስተያየቶች አብዛኛው በጥናቱ ትኩረት እንደተደረገባቸው ገልጸው፤ ሊወሰዱ የሚገባቸው ጥንቃቄዎቹን ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ ዳብሮ ጥናቱ እንደሚቀርብ ተናግረዋል። የባለሞያዎችን አስተያየት ተከትሎ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የመድረኩን መዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ቦርዱ በምርጫ መታዘብ ወቅት በሴቶች ላይ ትኩረት አድርገው በሚሠሩ ታዛቢ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የወጡ ሪፖርቶችን እንደሚያደንቅ ገልጸው፤ በዕለቱ ለቀረበው ጥናት ማካሄጃ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገውን ዩ. ኤን ዉመንንም እንዲሁ አመስግነዋል። ቦርዱ በቀጣይ ምርጫ “በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች” የትኞቹ ናቸው የሚለውን በሚገባ በመለየትና ሊወሰዱ የሚገቡ ርምጃዎችንም አስቀምጦ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚሠራ ተናግረዋል። ባለሞያዎቹ ያቀረቡት ጥናትም የምርጫ ቀን የሚታየው ሁነት ከምርጫው በፊት የነበሩ የባለድርሻ አካላት እንቅስቃሴ አጠቃላይ ውጤት መገለጫ እንደመሆኑ መጠን በጥናቱ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው፣ የበይነ መረቡ ዓለም ተፅዕኖም ቀላል ባለመሆኑ ጥናቱ እሱንም ቢያካትት የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል።

Share this post