Skip to main content

የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክቶ በቦርዱ የተሰጠው ውሳኔ ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብልጽግና ፓርቲ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ያደረገውን 1ኛ ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ለፓርቲው አሳውቋል።

በዚህም መሠረት የውሳኔው አንኳር ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

በፓርቲው በጉባዔው የተመረጡ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር የቦርዱ ታዛቢዎች በወቅቱ የምርጫው ውጤት ሲገለፅ መዝግበው ካቀረቡት ዝርዝር ጋር ልዩነት መኖሩን አረጋግጦ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ቦርዱ ምርጫውን ሲታዘቡ መዝግቦ የያዛቸው መሆናቸውን በመጨረሻ የወሰነ ሲሆን ስም ዝርዝራቸውንም ከውሳኔው ጋር አያይዞ ልኳል።

የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላትን በተመለከተም ተመርጠዋል ተብለው የቀረቡት የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላት በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፅ 74/3 ግልጽ፤ ነጻና ፍትሐዊ በሆነ በሚስጢር በሚሰጥ ድምጽ ያልተመረጡ እንዲሁም በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 23/1 መሠረት ጠቅላላ ጉባኤው ድምፅ ሰጥቶ የመረጣቸው ሳይሆን ለጠቅላላ ጉባዔው ስም ዝርዝራቸው ለጉባዔው የተገለፀ መሆኑ ጠቅላላ ጉባኤውን በታዘቡት የቦርዱ ታዛቢዎች ስለተረጋገጠ በ4 ወራት ጊዜ ውስጥ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላት ምርጫ እንዲያደርግ ቦርዱ ወስኗል፡፡

የፓርቲውን ህገደንብ አስመልክቶ የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴን አስመልክቶ፣ የቁጥጥር እና ኢንፔክሽን ጉባኤ አባላት አመራረጥ እና ስብጥርን አስመልክቶ፣ የጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች ዝቅተኛ ቁጥርን አስመልክቶ እና የፓርቲው ፕሬዘዳንት እና ምክትል ፕሬዘዳንት አመራረጥ እና እጩነት ሂደትን አስመልክቶ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ እንዲያሳውቅ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ፓርቲውን ወክለው ለምርጫ የሚሳተፉ አባላት እጩነት ሂደትን አስመልክቶ መመሪያ ይወጣል በሚለው የህገደንቡ አንቀጽ መሰረት መመሪያው እንዲወጣ እና ለቦርዱ እንዲቀርቡ ወስኗል።

ቦርዱ በኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፅ 161 እንደተደነገገው ቦርዱ በዚህ ህግ የተሰጡትን ሀላፊነቶችን ለመወጣት ያስፈልጋል ያላቸውን ተግባራት ስራ ላይ ለማዋል ይህን ፓርቲ ጨምሮ ማንኛውም ሰው የመተባበር ግዴታ (Duty to Cooperate) ቢኖርበትም ብልጽግና ፓርቲ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ ከመጋቢት 2 እስከ 4/2014 ዓ.ም. በቦርዱ የተመደቡ ባለሞያዎች ሂደቱን ለመቅረጽ በመከልከሉ ፓርቲው ይህ ተቀባይነት የሌለው ተግባር እንዳይደገም ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አስታውቋል። የውሳኔው ደብዳቤ ዝርዝር ለማግኘት እዚህ ላይ ይጫኑ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

መስከረም 02 ቀን 2015 ዓ.ም

Share this post