የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 1133/2011 ዓ.ም. እና በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም. መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመመዝገብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

በዚህም መሠረት በዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 66 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ ፓርቲነት ለመንቀሳቀስ የሚችለው በሕጉ መሠረት በቦርዱ ተመዝግቦ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሲያገኝ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በዐዋጁ አንቀጽ 66 ንዑስ አንቀጽ ሦስት መሠረት ለቦርዱ የዕውቅና ጥያቄ ለማቅረብና ፓርቲውን ለማስመዝገብ የሚያስፈልጓቸውን ተግባራት ለማከናወን ይችሉ ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ቦርዱ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ማመልከት ይችላሉ፡፡ ቦርዱም ጊዜያዊ ፈቃድ ለማግኘት በሕጉ የተቀመጡ መሥፈርቶችን አሟልተው ሲቀርቡ ለሦስት ወራት ብቻ የሚያገለግል ጊዜያዊ ዕውቅና ፈቃድ ይሰጣቸዋል። ከቦርዱ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ፈቃዱን መጠቀም የሚችሉት በዐዋጁ መሠረት ፓርቲውን ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ተግባራትን ለማከናወን ብቻ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ይሁንና አልፎ አልፎ ፓርቲ ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ተግባራትን ለማከናወን ብቻ ከቦርዱ ጊዜያዊ ፈቃድ የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጉ መሠረት ለምዝገባ የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን አሟልተው ለቦርዱ በማቅረብ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ባላገኙበት ሁኔታ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ሲሣተፉና የተለያዩ ቃለ ምልልሶችን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡

በመሆኑም ቦርዱ በሕጉ መሠረት ጊዜያዊ ፈቃድ የሚሰጠው ፓርቲ ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ተግባራትን ለማከናወን ብቻ መሆኑን እያሳወቅን፤ ከቦርዱ ጊዜያዊ ፈቃድ ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለቦርዱ የምዝገባ ጥያቄ አቅርበው በሕጉ መሠረት ማሟላት ያለባቸውን በማሟላት የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሳይሰጣቸው ወደተለያዩ እንቅስቃሴዎች መግባት የማይችሉ መሆኑን ቦርዱ ያሳውቃል፡፡ በተጨማሪም የሚመለከታቸው ተቋማትና አካላትም ለሦስት ወራት ጊዜያዊ ፈቃድ ስለተሰጣቸው ብቻ ከቦርዱ በሕጋዊ ተመዝግበው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ካላገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ግንኙነቶችን ማድረግ የማይችሉ መሆኑን ቦርዱ ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ማስታወቂያ
ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም.