Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ተኛው አጠቃላይ የምርጫ ሂደት ላይ የተደረገ የግምገማ ውጤት እንዲሁም የተገኙ ትምህርቶችን ማስተዋወቂያ እና ማጠናቀቂያ ዐውደ-ጥናት ዛሬ ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ቦርዱ የ6ተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ተከትሎ በምርጫ ሂደቱ ላይ ከተገበራቸው የተለያዩ ተግባራት የተገኙ ትምህርቶችን የመሠነድ ተግባር ሲያከናውን የቆየ ሲሆን በሂደቱ የምርጫ ቦርድ አባላት፣ ሠራተኞች፣ የክልል ጽ/ቤት ሃላፊዎች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዛቢ ቡድኖች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የፊደራል እና የክልል የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፍትሕ አካላት፣ የፀጥታ እና ሕግ አስከባሪ አካላት በተጨማሪም ከአጋዥ ድርጅቶች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ፎር ኤሌክቶራል ሲስተምስ (IFES) እና ዩሮፕያን ሴንተር ፎር ኤሌክቶራል ሰፓርት (ECES) በአጠቃላይ ከ400 በላይ ተሳታፊዎች ከተለያዩ የባላድርሻ አካላት በማካተት በየካቲት እና በመጋቢት ወራት ላይ ከ50 በላይ አነስተኛ የቡድን ውይይቶች፣ የምክክር መድረኮች፣ የቃል እና የጽሑፍ መጠይቆች ተከናውነዋል፡፡

የግምገማ ሂደቱ የተካሄደበት ሥነ-ዘዴ ዓለም ዐቀፋዊ ተቀባይነት ያላቸው ዋና ዋና የምርጫ መርሆችን ማለትም ነፃነት፣ ገለልተኝነት፣ ግልጽነት፣ የሙያ ብቃት አካታችነት እና ዘለቄታዊነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡ በሂደቱም ትኩረት የተደረገባቸው ዋና ዋና የምርጫ ዑደቶች የሆኑት የሕግ እና ተቋማዊ መዋቅር፣ የምርጫ ኦፕሬሽን ዕቅድ እና ትግበራ፣ የመራጮች ምዝገባ፣ የዕጩዎች ምዝገባ፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ የድምፅ አሰጣጥ እና ቆጠራ፣ የውጤት አያያዝ፣ የምርጫ ክርክር አፈታት፣ ምርጫን የመታዘብ ሂደት፣ የመራጮች ትምህርት፣ የሥርዓተ ፆታና አካታችነት የመሳሰሉት ጉዳዮች ናቸው፡፡

በዚህ ለሁለት ቀን በሚቆየው ዐውደ-ጥናት ላይ የተገኙ ግኝቶችን፣ ተግዳሮቶችን እና ውጤታማ ተሞክሮዎችን በማካተት ተተንትኖ በዛሬ እና በነገው እለት ከላይ የተጠቀሱት ባለድርሻ አካላት በተከኙበት ይቀርባል፡፡ በዐውደ-ጥናቱ ላይ የተገኙ ትምህርቶችና ተግባራዊ የመፍትሄ ሀሳቦች ማጠቃለያ ሪፖርት ቦርዱ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን ሪፓርቱ በቀጣይ ለሚያከናወኑ ምርጫዎችም ሆነ አጠቃላይ ተግባራት ገንቢ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም

Share this post