Skip to main content

ማብራሪያ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 26 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ ባስታወቀው መሰረት የፓርቲዎች የጠቅላላ ጉባኤ ሲያካሂዱና ለማካሄድም ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዚህም መሰረት የፓርቲዎች የጠቅላላ ጉባኤ ሁኔታ ማጠቃለያ የሚከተለውን ይመስላል።

ጠቅላላ ጉባኤ ያካሄዱ ፓርቲዎች

  1. ብልጽግና ፓርቲ
  2. ህዳሴ ፓርቲ
  3. ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ
  4. የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ

ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ በጊዜ ገደቡ መሰረት ቀን ያሳወቁ ፓርቲዎች

  1. ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( መጋቢት ሰባት እና ስምንት)
  2. የአርጎባ ብሔረ ሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ( መጋቢት ስምንት)
  3. የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ( መጋቢት 7)

ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቀው ቦርዱ ምላሽ የሰጣቸው ፓርቲዎች

  1. የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ - በአንዳንድ የሀገሪቷ ክልሎች የፀጥታ ችግር ስላለ የጠቅላላ ጉባኤ አባላቱ በተጠቀሰው ቀን ለመድረስ ችግር እንደሚፈጥባቸው ገልጾ ለመጋቢት 30/2014 ዓ.ም. እንዲያካሂድ ጠይቆ ተፈቅዶለታል
  2. የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ - አብዛኞቹ አባላቶች የሚገኙት በአማራና በኦሮሚያ ክልል በመሆኑ በክልሎቹ ካለው የፀጥታ ችግር የተነሳ እንዲሁም ከመንገዱም ሥጋት ጋር አስቸጋሪ ስለሆነበት እስከ ሚያዝያ 2/2014 ድረስ እንዲያካሂድ ጠይቆ ተፈቅዶለታል
  3. የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ- የሕትመት ሥራዎች ስላልደረሱ፣ የስብሰባ አዳራሽ ከፍተኛ ወጭ መጠየቅ ዝግጅት ተጨማሪ ጊዜ በመጠየቁ መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዲያካሂድ ጠይቆ ተፈቅዶለታል
  4. ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ - ለጉባኤው አስፈላጊ የሆኑ የፋይናንስ እና ሎጂስቲክስ ጉዳዮች አስቻይ ባለመሆናቸው ገልጾ መጋቢት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዲያካሂድ ጠይቆ ተፈቅዶለታል
  5. የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ- የፓርቲው አባላቶች በእስር ላይ ስለሚገኙ፣ የፓርቲው የክልል ጽህፈት ቤቶች ተዘግተው ስለሚገኙ፣ በግጭቶች ምክንያት በበርካታ የኦሮምያ ዞኖች እና ሌሎ ች ክልሎች ውስጥ ያለው ሁኔታ ያልተረጋጋ ስለሆነ በሚል አቤቱታ አቅርቦ መጋቢት 17 እና 18/2014 ዓ.ም. እንዲያካሂድ ተፈቅዶለታል
  6. አዲስ ትውልድ ፓርቲ- የፓርቲው ሊቀመንበር ታስረው በነበሩበት ወቅት የፓርቲው የዕለት ተዕለት ሥራ የተስተጓጎለ በመሆኑ፣ በግጭቶች ምክንያት በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ያለው ሁኔታ ያልተረጋጋ ስለሆነ ሚያዝያ 15/2014 ለማድረግ ጠይቆ ቦርዱ እስከ ሚያዝያ 8/2014 ድረስ ቢሰጥ በቂ ጊዜ ነው በማለት ወስኗል።
  7. የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት - በግጭቶች ምክንያት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ሌሎች ክልሎች ውስጥ ያለው ሁኔታ ያልተረጋጋ ስለሆነ እና የትራንስፖርት ችግር በመኖሩ ከሚያዝያ 29-30/2014 ለማድረግ ጠይቆ እስከ ሚያዝያ 8/2014 ድረስ በቂ ጊዜ ነው በማለት ቦርዱ ወስኗል።
  8. የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ- በግጭቶች ምክንያት በበርካታ የኦሮምያ ዞኖች እና ሌሎች ክልሎች ውስጥ ያለው ሁኔታ ያልተረጋጋ ስለሆነ እና የሎጅስቲክስና የፋይናንስ ችግር በማጋጠሙ ከመጋቢት 30 - ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ለማካሄድ ጠይቆ ተፈቅዶለታል።
  9. ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ- ፕሮግራምና ደንቡን ለማሻሻል፣ ለመከለስና ለማስተካከል፣ የኦዲት ስራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ በማስፈለጉ፤ ለጉባኤው ከሚያስፈልገው በጀት አንፃር የፋይናንስ እጥረት በማጋጠሙ መጋቢት 25/2014 እንዲያካሂድ ጠይቆ ተፈቅዶለታል
  10. የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ - ቀደም ብሎ ጠቅላላ ጉባኤውን መጋቢት 11/2014 እንደሚያካሂድ በማሕበራዊ ትስስር ገፅና ለፓርቲው መዋቅር ያሳወቀ በመሆኑ እና ዝግጅቶችም በዚያው ቀን በመታቀዳቸው መጋቢት 11/2014 እንዲያካሂድ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡
  11. የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ- የፓርቲው አመራር፣ አባላት እና ደጋፊዎች እስር ላይ መቆየት፣ ከሥራ መፈናቀል እና ማዋከብ ያጋጠማቸው መሆኑን አቤቱታ አቅርቦ እስከ ሚያዝያ 02/2014 ዓ.ም.እንዲያካሂድ ጠይቆ ተፈቅዶለታል።
  12. ቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ - መተከል ዞን ካለው የፀጥታ ችግር አንፃር አብዛኛው የጉባኤ ተሳታፊ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡና ትራንስፖርቱ በእጀባ ስለሆነ መጋቢት 10 እና 11/2014 እንዲሆን በጠየቀው መሰረት ተፈቅዶለታል።

በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ባለ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር የተነሳ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ እንደማይችሉ ጠቅሰው የተፈቀደላቸው

  1. የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
  2. ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲያዊ ሉአላዊነት
  3. የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
  4. አፋር ህዝቦች ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ

ለቦርዱ የማራዘም ጥያቄ አቅርበው ውሳኔ ያልተሰጠባቸው እና ምክንያታቸው እየታየ ያለ

  1. የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር
  2. የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
  3. የሲዳማ አርነት ንቅናቄ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

መጋቢት 07 ቀን 2014 ዓ.ም

Share this post