የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስከረም 20 ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ካከናወነባቸው ቦታዎች መካከል ድጋሚ ምርጫ እንዲከናወን የተወሰነበት የምስቃን እና ማረቆ 2 ምርጫ ክልል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። በዚሁ ምርጫ ክልል የመራጮች ድምጽ አሰጣጥ በሰላም የተጠናቀቀ ቢሆንም ቦርዱ በእለቱ የተለያዩ አቤቱታዎችን ሲቀበል የዋለ ሲሆን በተጨማሪም ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ድምጽ ቆጠራ ተጠናቆ ለምርጫ ክልል ከደረሰ በኋላ ምርጫ ክልሉ ሃላፊዎች በጸጥታ ስጋት የተነሳ ውጤት ድመራን ማከናወን እንደሚቸግራቸው ሪፓርት አድርገዋል፣ ቦርዱም ሁኔታውን ገምግሞ የምርጫ ክልል ላይ የውጤት ድመራን ማከናወን አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ተረድቷል።

በመሆኑም በምርጫ ክልል ደረጃ ያለው የውጤት ድመራ እነዲቋረጥ እና የድመራ ሂደቱ በቦርዱ ኦፕሬሽን መአከል በአዲስ አበባ እንዲከናወን ወስኗል። በዚህም መሰረት ቦርዱ ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የድምጽ አሰጣጥ ቁሳቁሶችን በሙሉ ወደ ማእከል የሚያጓጉዝ ሲሆን ይህ ተግባራዊ እስኪደረግ ድረስ ቁሳቁሶች በህጉ መሰረት ታሽገው እንዲቀመጡ መመሪያ አስተላልፏል። የእጩዎች ወኪሎች እና የፓርቲ ወኪሎች ውጤት ድመራው በማእከል በሚከናወንበት ወቅት ወኪሎቻቸውን በመላክ መታዘብ ይችላሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

መስከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም