የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንትና መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሐረሪ/ በሶማሌ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የተወካዮች ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤት እና የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልልነት ህዝበ ውሳኔን በሰላም ማጠናቀቁ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት በዛሬው እለት

  • በሐረሪ ከሚገኙ 231 ጣቢያዎች 152ቱ፣ በሶማሌ ከሚገኙ 3957 ጣቢያዎች 1327ቱ፣ በደ/ብ/ብ/ህ ክልል ከሚገኙ 2800 ጣቢያዎች 1678ቱ ከምርጫ ጣቢያ ቆጠራ አጠናቀው እና ይፋ አድርገው ለምርጫ ክልልሎቻቸው ውጤቶችን አስረክበዋል። ከሐረሪ ክልል ውጪ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የሰጧቸው ድምጾችም ወደሃረሪ የተላኩ ሲሆን በምርጫ ክልል ባለው ውጤት ድመራ ውስጥ የሚካተቱ ይሆናል። ምርጫ ክልሎችምርጫ ጣቢያዎን በማገዝ ውጤቶችን ተቀብለው የማዳመር ስራን ለመስራት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
  • የህዝበውሳኔ ውጤቶች ይፋ የተደረጉ ሲሆን ውጤቶች ይፋ ተደርገው ወደ ቦንጋ ማስተባበሪያ ቢሮ መድረስ ጀምረዋል።
  • ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድምጽ መስጫው እለትም ሆነ በዛሬው እለት ሂደቱን በተመለከተ ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች እና እጩዎች 42 አቤቱታዎችን ተቀብሏል። እነዚህ አቤቱታዎችን ያቀረቡት ስምንት የፓለቲካ ፓርቲዎች እና ዘጠኝ የግል እጩዎች ናቸው። የአቤቱታዎቹ አይነትም የእጩ/ፓርቲ ወኪሎች መከልከል፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች የአሰራር ጉድለት፣ የእጩዎች መንገላታትን፣ የምርጫ አፈጻጸም አሰራሮች በትክክል አለመከናወን… የመሳሰሉ ይገኙበታል። ቦርዱ በድምጽ መስጫው ቀን መፍታት የሚቻሉትን ችግሮች ከስር ከስር ለመፍታት ሙካራ ያደረገ ሲሆን አልተፈቱም በሚል የቀረቡ አቤቱታዎችን እያየ ይገኛል።
  • 11 የሲቪል ማህበራት ከ3700 በላይ ታዛቢዎችን ለማሰማራት መታወቂያ ወስደው ዝግጅቶችን አድርገው የነበረ ሲሆን 2569 ታዛቢዎች በትላንትናው እለት ተሰማርተው እንደነበር ተረጋግጧል። ከነዚህም መካከል 263 ቱ በሐረር፣ 877ቱ በሶማሌ፣ 1424ቱ በደ/ብ/ብ/ህ/ክ የታዘቡ ሲሆን አምስት ታዛቢዎች ድሬደዋ ሁለት ጣቢያዎች ላይ ይከናወን የነበረውን ምርጫ ታዝበዋል። ሲቪል ማህበራቱም የተከታተሏቸውን ትዝብቶች ለቦርዱ ያደረሱ ሲሆን ( የመታዘብ መከልከል፣ የስርአት ችግሮች፣ የመራጮች ማንነት ማሳወቂያ ጋር የተገናኙ ችግሮች፣ የመራጮች እድሜ …ወዘተ) ቦርዱም ከስር ከስር ችግሮቹን ሲፈታ ውሏል። በእለቱ በሲቪል ማህበራት በኩል በአጠቃላይ 14 አቤቱታዎች ለቦርዱ ቀርበዋል።

ቦርዱ ውጤት ቆጠራን ማረጋገጥን እና ይፋ ማድረግን በተመለከተ ተከታታይ መረጃዎችን በሚቀጥሉት ቀናትም የሚሰጥ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም