የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ ባልተሰጠባቸው ቀሪ ምርጫ ክልሎች እና የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ሐሙስ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲከናወን መወሰኑ ይታወቃል። በዚህም መሰረት በእለቱ የተመዘገቡ ዜጎች ሁሉ ድምጻቸውን ለመስጠት ይችሉ ዘንድ እና የደምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ያለምንም የጸጥታ ችግር ይከናወን ዘንድ ቦርዱ የሚከተሉት ተግባራዊ እንዲሆኑ የምርጫ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 161 የመተባበር ግዴታ መሰረት ለመንግስታዊ እና ለማንኛውም መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት ያሳውቃል።

በዚህም መሰረት በሐረሪ ክልል፣ በሶማሌ ክልል፣ በደ/ብ/ብ/ህ ክልል በምእራብ ኦሞ ዞን፣ በደቡብ ኦሞ ዞን፣ በቤንች ሸኮ ዞን፣ በሸካ ዞን፣ በጌዲዮ ዞን፣ በሃድያ ዞን፣ በጉራጌ ዞን፣ በጋሞ ዞን፣ በካፋ ዞን፣ በወላይታ ዞን ፣ በዳውሮ ዞን፣ በባስኬቶ ልዩ ወረዳ እና በኮንታ ልዩ ወረዳ

- ዜጎች እለቱን ለድምጽ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ ከላይ በተጠቀሱት ክልሎች እና ዞኖች የሚገኙ የፌዴራል እና የክልል መንግስታዊ ተቋማት መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ስራ ዝግ እንዲያደርጉ

- ዜጎች እለቱን ለድምጽ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ ከላይ በተጠቀሱት ክልሎች እና ዞኖች የሚገኙ ማንኛውም መንግስታዊ ያልሆኑ እና የግል ተቋማት በተመሳሳይ መስከረም 20 ቀን 2014 ዝግ እንዲያደርጉ እያሳወቀ

- የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ የእለት ተእለት አገልግሎት ሰጪዎች (ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፓርት አገልግሎት …ወዘተ) በዝግ ቀናት የሚያደርጉትን አገልግሎት በተመሳሳይ ማከናወን የሚችሉ ሲሆን የመተባበር ግዴታው እነዚህን ተቋማት እንቅስቃሴ መዘጋት አያስገድድም።

- የትራንስፓርት አገልግሎት በተለመደው መንገድ የሚቀጥል ቢሆንም በተጠቀሱት ክልሎች እና ዞኖች ዜጎች ድምጽ ከመስጠት ውጪ ከፍተኛ እንቅስቃሴን የሚፈልጉ ሁነቶችን እና እቅዶችን እንዳይዙ እና እንቅስቃሴያቸውን ድምጽ ለመስጠት ብቻ እንዲያደርጉ ቦርዱ ያበረታታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም