የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው ሀገር ዐቀፍ ምርጫን ለመዘገብ ፍላጎት ላላቸው ብዙኃን መገናኛ አካላት ጥሪ አድርጎና በደንቡ የተደነገጉትን ቅድመ ሁኔታዎችን ቅጽ በማስሞላት የዘገባ ባጅ በፍላጎታቸው ልክ እና በተለያየ ጊዜ መስጠቱ ይታወቃል። ይህም የዘገባ ባጅ የ6ኛው ሀገር ዐቀፍ ምርጫ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንደሚያገለግልና በምርጫ ወቅትም ከምርጫ ጣቢያዎች በ200ሜ ዙሪያ ተገኝቶ ለመዘገብ የግድ የሚያስፈልግ መሆኑን በቦርዱ የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች ከመግለጽ ባሻገር፤ በህግ የተደነገገ መስፈርት ነው።

ስለሆነም የ6ኛው ሀገር ዐቀፍ ምርጫ አካል የሆነው የመስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ምርጫንም ለመዘገብ እንዲሁ ለብዙኃን መገናኛ የታደለውን ባጅ መያዝ የግድ መሆኑን በድጋሚ ለማሳወቅ እንወዳለን። በምርጫ ወቅት ከምርጫ ጣቢያዎች በ200ሜ ዙሪያ ተገኝቶ ለመዘገብ የቦርዱን የዘገባ ባጅ ፊት ለፊት ማሳየት በመመሪያውም የተደነገገ ሲሆን፤ ይህን የማያደርግ የዘገባ ባለሞያ (የፎቶ ባለሞያን ጨምሮ) ተጠያቂ የሚሆን ሲሆን የምርጫ አስፈጻሚዎችም ባጅ ላልያዙ ዘጋቢዎች ትብብር የማድረግ ግዴታ እንደሌለባቸው ለመግለጽ እንወዳለን።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ማስታወቂያ
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም