የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለድምፅ መስጫና ለኦፕሬሽን ሥራዎች የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ከማዕከል ወደ ምርጫ ክልሎች አሰራጭቶ አጠናቀቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በሐረሪ ክልል፣ በሶማሌ ክልል እና በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል ለሚያካሂደው ምርጫና ሕዝበ ውሣኔ፤ ለድምፅ መስጫና ለኦፕሬሽን ሥራዎች የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ከማዕከል ወደ ምርጫ ክልሎች አሰራጭቶ አጠናቀቀ። ሥርጭቱ ዐርብ መስከረም 07 ቀን 2014 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን ሐረሪ ክልል፣ ሶማሌ ክልል እና ደ/ብ/ብ/ሕ ክልል ላይ የሚሠራጩትን ቁሳቁሶች የጫኑ መኪኖች አዲስ አበባ ከሚገኘው የቦርዱ ጊዜያዊ መጋዘን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደየጫኑበት ምርጫ ክልል ተንቀሳቅሰው ጨርሰዋል። በአዲስ አበባና ቅርብ አካባቢዎች ለሐረሪ ተወላጆች ለተከፈቱት ምርጫ ጣቢያዎች የሚሠራጩትን ቁሳቁሶች ደግሞ የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች መድረስ ያለበትን የጊዜ እርዝማኔ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የሚጠናቀቅ ይሆናል።