Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሚካሄደው ምርጫ ዝግጅት የመስክ ጉብኝት አደረጉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች ከጳግሜ 2 እስከ ጳግሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ምርጫ የሚካሄድባቸውን አካባቢዎች ማለትም ሶማሌ ክልል፣ ሐረሪ ክልል እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የመስክ ጉብኝት እና ውይይቶችን አከናውነዋል። በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የተመራው ቡድን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መቀመጫ ከተማ ላይ የክልሉን ርዕሰ-መስተዳደር፣ የዞን አመራሮችንና በአካባቢው ላይ የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎችን አግኝቶ የመስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ምርጫን የተመለከቱ አጠቃላይ የምክክር መድረክ አካሂዷል። ከድምጽ መስጫ ቀኑ በተጨማሪ በተመሳሳይ መስከረም 20 ለሚካሄደው ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ውይይት ተደርጓል።

በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለና በቦርዱ አመራር አባል በሆኑት ብዙወርቅ ከተተ የተመራው ሁለተኛው ቡድን የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መስተዳደርና በአካባቢው ላይ የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎችን በክልሉ ዋና ከተማ አግኝቶ አወያይቷል። በጀጎል ልዩ ምርጫ ክልል እና በጀጎለ ዙሪያ እና ሁንደኔ ምርጫ ክልል ያሉ መደበኛና ልዩ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በመካሄድ ላይ የነበረውን የመራጮች ምዝገባ በመጎብኘት የምርጫ አስፈጻሚዎችንና የዞን አስተባባሪዎችን አነጋግረዋል። ከዚህም በተጨማሪም የሐረሪና የድሬዳዋ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ጎብኝተዋል።በድሬዳዋ ከተማ የመራጮች ምዝገባ የሚከናወንባቸው ውስን ምርጫ ጣቢያዎችም በሁለተኛው ቡድን ጉብኝት ከተደረገባቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ።

ሦስተኛው ቡድንም እንዲሁ የቦርድ አመራር አባል በሆኑት አበራ ደገፋ (ዶ/ር) እና ፍቅሬ ገ/ሕይወት የተመራ ሲሆን፤ ቡድኑ በቆይታው ከላይ እንደተጠቀሱት ሁለት ቡድኖች ሁሉ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መስተዳደርና በአካባቢው ላይ የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎችን በክልሉ ያወያየ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም በአካባቢው በመካሄድ ላይ የነበረውን የመራጮች ምዝገባ በመጎብኘት የምርጫ አስፈጻሚዎችን እና የዞን አስተባባሪዎችን አነጋግሮዋል። በሁሉም ጉብኝቶች ከምርጫ ቦርዱ ስራዎች በተጨማሪ ከመንግስት ሃላፊዎች ጋር መጪውን ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ እየተሰሩ ስላሉት የጋራ ስራዎች ውይይቶች ተደርገዋል።

Share this post