Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ላይ ለሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች የሚውለውን የነፃ ዐየር ሰዓት ድልድል አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በመጪው መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ላይ ለሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች የሚውለውን የነፃ ዐየር ሰዓት ድልድል አካሄደ። የዐየር ሰዓት ድልድሉ መመሪያውን መሠረት አድርጎ፤ በሶማሌ ክልል፣ በሐረሪ ክልል እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ለሚወዳደሩ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎችና 106 የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች የቀረበ ሲሆን፤ ይህውም በሦስት ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ በአራት ቴሌቪዥንና በሁለት ጋዜጦች ላይ ተከናውኗል።

በድልድሉ በቴሌቪዥን 39 ሰዓታት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሲቀርብ ለግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ደግሞ 26 ሰዓታት ከግማሽ ሰዓት ቀርቧል፣ በሬዲዮ 32 ሰዓታት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሲቀርብ ለግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ደግሞ 26 ሰዓታት ከግማሽ ሰዓት ቀርቧል፣ በጋዜጦችም እንዲሁ በአጠቃላይ 45 ዐምድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ቀርቧል። የነፃ የዐየር ሰዓቱ ከጷግሜ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም ተፈጻሚ ይሆናል። በመሆኑም የፓለቲካ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋናው ቢሮ የድልድል ሰአታቸውን መውሰድ የሚችሉ ሲሆን ድልድሉ የተከናወነው ከዚህ በፊት በነበረው የእጣ ቴክኖሎጂ መሰረት ነው።

Share this post