የሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የጋራ ምክር ቤት ምሥረታ ተካሄደ
ዛሬ ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የጋራ ምክር ቤት ምሥረታ ጉባዔ ተካሄደ። የቦርዱ አመራር አባላት የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ፤ አበራ ደገፋ (ዶ/ር)፣ ፍቅሬ ገ/ሕይወት፣ ውብሸት አየለ እንዲሁም የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ ሴቶች የተሣተፉበትን ይህንን ጉባዔ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ሴቶች በፓለቲካ ያላቸው ተሣትፎ እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ገልጸው ቦርዱም ይህን እንዲሻሻል ይርዳ ዘንድ የተለያዩ ሥራዎችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለመሥራት ቢሞክርም ከሚፈለገው ለውጥ አንጻር ግን ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ገልጸዋል። የጋራ ምክር ቤቱን የመመሥረት ውጥን ሁለት ዓመታት እንዳሳለፈና ትልቅ ፋይዳም እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የምክትል ሰብሳቢውን ንግግር ተከትሎ በቦርዱ የሥርዓተ- ፆታና ማኅበራዊ አካታችነት ክፍል አስተባባሪነት መድርኩ ለተሣታፊዎች ክፍት የተደረገ ሲሆን፤ ተሣታፊዎቹም ቦርዱ ይህን ጉባዔ ማዘጋጀቱን በትልቅ ደስታ እንደሚቀበሉትና ትልቅ አስተዋፆ እንደሚኖረው ገልጸው፤ ምክር ቤቱን ለመመሥረት በቀረበው ረቂቅ የአሠራር ሥርዓት ሠነድ ላይ ቢሻሻሉ ያሏቸውን ነጥቦች በዝርዝር አስረድተዋል። ተሣታፊዎቹ ያነሧቸው አስተያየቶችና ቢሻሻሉ ያሏቸውን ነጥቦች መሠረታዊነት ያላቸው እንደሚሻሻሉ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ የገለጹ ሲሆን፤ የቦርድ አመራር አባል የሆኑት አበራ ደገፋም (ዶ/ር) ከሕግ አንጻር ቢሻሻሉ ተብለው የተጠቀሱት ነጥቦች ያላቸውን አግባብነት ምን እንደሚመስል አስረድተዋል። የሴት ፓለቲካ ፓርቲ አባላት የጋራ ምክር ቤትም ሴት አባላት እንደ ፓለቲከኝነታቸው በጋራ ከሴቶች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ አገራዊ ጉዳዮቹን የሚያዩበት ሲሆን ይህ የቃልኪዳን ሰነድ መፈረም ለጋራ የሴቶች የፓለቲካ ስራ መነሻ ይሆናል የሚል ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የጋራ ምክር ቤቱን የመመሥርቱ ጉዳይ የዘገየ እንደሆነ የጠቀሱት የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ፤ ሀገር ዐቀፍ ምርጫው ላይ ለሴት ዕጩዎች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንደተሰጡና በሥልጠናውም ወቅት የተሰበሰቡትም አስተያየቶች የምክር ቤቱን መመሥረት አስፈላጊነት የሚጠይቁ እንደነበሩ አስታውሰዋል። በመጨረሻም ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የጋራ ምክር ቤት የሥራ ግንኙነትና በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር ሥርዓት የቃል ኪዳን ሠነድ ላይ የተጠቀሱት አስተያየቶች ተሻሽለው ከተነበበ በኋላ የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ተፈጽሟል። በጉባዔው መጨረሻም በቦርዱ የፖለቲካ ሥራ ክፍል አስተባባሪነት የምክር ቤቱ ጊዜያዊ አመራሮች የተመረጡ ሲሆን፤ በምርጫውም ነቢሃ መሃመድ ሊቀ-መንበር፣ ቆንጂት ብርሃኑ ምክትል ሊቀ-መንበር እንዲሁም መሊሃ ጂሃድ ፀሃፊ ሆነው ተመርጠዋል።