የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሃሴ 17 ቀን 2013 ቀን ባሳወቀው መሰረት የመስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም የድምፅ አሰጣጥ በሚከናወንባቸው የተለያዩ ምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ ሁኔታን አስመልከቶ ውሳኔዎች አሳለፏል። ከዚያም መካከል ተጀምሮ የነበረው የመራጮች ምዝገባ የሚቀጥልባቸው፣ የመራጮች ምዝገባ እንደአዲስ የሚከናውንባቸው እና የመራጮች ምዝገባ የማያስፈልግባቸው የምርጫ ክልሎችን ማሳወቁ ይታወሳል።

ከነዚህም መካከል የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አንዱ ሲሆን በክልሉ እየተከናወነ በነበረው የመራጮች ምዝገባ ላይ በቀረበ ከፍተኛ አቤቱታ እና ማስረጃ መሰረት ቦርዱ ማጣራት አስፈላጊ ነው ብሎ በማመኑ የአጣሪ ቡድን ተልኮ ውጤቱ እስኪወሰን ድረስ የመራጮች ምዝገባ መቋረጡ ይታወሳል። በዚህም መሰረት

1. አጣሪ ቡድን አዘጋጅቶ በ10 ምርጫ ክልሎች በማሰማራት

2. የአጣሪ ቡድኑን ሪፓርት በመገምገም

3. የአጣሪ ቡድኑን ሪፓርት ለፓለቲካ ፓርቲዎች በማቅረብ እና የተሰጠውን የውሳኔ ሃሳብ በማገናዘብ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እንዲደገም ፣ በቀሪዎቹ በተቋረጠባቸው ደግሞ ለ5 ቀናት ቀሪ ምዝገባ ተከናውኖ እንዲጠናቀቅ ወስኗል። እነዚህም የተወሰነባቸው ቦታዎች በዝርዝር ከነምክንያታቸው የሚከተሉት ናቸው።

የመራጮች ምዝገባ ሙሉለሙሉ እንዲደገምባቸው የተወሰነባቸው

• የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች

- ጅጅጋ 1 ምርጫ ክልል -

- ጅጅጋ 2 ምርጫ ክልል

ምክንያት

በጅጅጋ 1 እና ጅጅጋ 2 የምርጫ ክልሎች የአጣሪ ቡድኑ በምርጫ ክልሎቹ ባደረገው ማጣራት የምርጫ ካርድ በገንዘብ እየተሸጠ እና በሰዎች እጅ ብዙ ካርዶች ያሉ መሆኑን ከምስክሮች በመስማቱ፣ ምርጫ አስፈጻሚዎችም የምርጫ ካርድ ሲሸጡ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በህግ እየታየ በመሆኑ፣ የተለያዩ የፓለቲካ ፖርቲዎች እጅ የመራጮች ካርድ በመገኘቱ ከዚህም በተጨማሪ በአጣሪ ቡድኑ የተሰሙ ምስክሮች እንዳስረዱት ምዝገባው በሚካሄድበት ወቅት ህጉን ተከትሎ አለመደረጉን በመረጋገጡ በተለይ ደግሞ በምስክር ምዝገባ ሲከናወን ከፍተኛ የአሰራር ጥሰት በመሆኑ ፍትሃዊ ምርጫን ለማከናወን አስቸጋሪ መሆኑ በአጣሪ ቡድኑ በመገለጹ

• የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች

- ቀብሪደሃር ከተማ ምርጫ ክልል

- ቀብሪደሃር ወረዳ ምርጫ ክልል

ምክንያት

ተወዳዳሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች አባላትና ደጋፊዎች በመሆናቸው ምክንያት ካርድ እንዳይወስዱ የተከለከሉ መኖራቸው እና በምርጫ ክልሉ የሚወዳደሩ ሁሉም የፓለቲካ ፓርቲዎች ካርድ ከወሰዱ መራጮች እጅ የመራጮች ካርድ ሰብስበው መያዛቸው በማጣራቱ ሂደት ተገልጿል፣ አጣሪ ቡድኑ ምዝገባው ይቀጥል የሚል ሃሳብ ቢያቀርብም ቦርዱ የተመዘገቡ መራጮች ካርድ ተሰብስበው መገኘታቸው ህገወጥ በመሆኑ እንዲሁም መሰረታዊ የሆነውን የድምፅ ሚስጥራዊነት መርህ የሚጋፋ በመሆኑ የመራጮች ምዝገባ እንዲደገም ወስኗል።

- መኢሶ ምርጫ ክልል

- አፍደም ምርጫ ክልል

ምክንያት

ቀድሞ የመራጮች ምዝገባ በፀጥታ እናሌሎች ምክንያቶች ሳይከናወንባቸው በመቅረቱ በምርጫ ክልሎቹ የመራጮች ምዝገባ ይከናወናል።

የመራጮች ምዝገባ የሚደገምባቸው በተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች

1. ዋርዴር ምርጫ ክልል ውስጥ አዶ ቀበሌ - 1 ምርጫ ጣቢያ እና ኤልድብር ቀበሌ - 2 ምርጫ ጣቢያዎች

ምክንያት

የመራጮች ምዝገባ ቀድሞ በሚከናወንበት ወቅት አለመደረጉ በመገለጹ በአሁኑ ምዝገባ እንደአዲስ እንዲከናወን በመወሰኑ

2. ፊቅ ምርጫ ክልል -01 ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ 01 – 1 ምርጫ ጣቢያ

ምክንያት

በዚህ ምርጫ ጣቢያ የመራጮች ካርድ በምርጫ ጣቢያው ወጥቶ ተሰብስቦ በመገኘቱ ፣ እንዲሁም በቀሪ ላይ ምንም ነገር ባለመሞላቱ በዚህ ጣቢያ ላይ የተደረገው የመራጮች ምዝገባ የህግ ጥሰት የተፈጸመበት መሆኑን የአጣሪ ቡድኑ ሪፓርት ያደረገ እና የውሳኔ ሃሳብም ያቀረበ በመሆኑ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባው አንዲደገም ወስኗል።

3. ገላዴን ምርጫ ክልል - 1 ምርጫ ጣቢያ

ምክንያት

የመራጮች ምዝገባ ካርዶች በተወዳዳሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች መሰብሰባቸው፣ በቀሪ ካርዶች ላይም መረጃዎች በሚገባ አለመሞላታቸው በመታየቱ

4. ጎዴ ከተማ ምርጫ ክልል - 4 ምርጫ ጣቢያዎች

ምስራቅ ኢሜ ምርጫ ክልል- 3 ምርጫ ጣቢያዎች

ቤራኖ ምርጫ ክልል - 3 ምርጫ ጣቢያ

ምክንያት

በአጣሪ ቡድኑ የመራጮች ምዝገቦች በሚታዮበት ወቅት ከፍተኛ የአመዘጋገብ ችግሮች በመታየታቸው እና በነዚህ ጣቢዎች ላይ ያለው የመራጮች ምዝገባ ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጥ ሆኖ ባለመገኘቱ

ማስታወቂያ
ነሀሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም