የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሚካሄደው ድምፅ አሰጣጥ የመራጮች ምዝገባ በሚከናወንባቸው ቦታዎች የአስፈጻሚዎች ስልጠናዎችን አከናወነ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሚካሄደው ድምፅ አሰጣጥ የመራጮች ምዝገባን ለማከናወን ዝግጅቶቹን እያጠናቀቀ ነው። በዚህም መሰረት ለሁለት ተከታታይ ቀናት ማለትም ነሐሴ 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ.ም ለሐረሪ ክልል፣ ነሐሴ 23 እና 24 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ ለሶማሌ ክልል እና ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ለመራጮች ምዝገባ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠናዎችን ሰጥቷል።
የምርጫ የሕግ-ማዕቀፎች፣ የምርጫ ጣቢያ አደረጃጀት፣ የመራጮች ምዝገባ ፅንሰ ሃሳብና መሥፈርቶች፣ ለኮቪድ መከላከል ሊወሰዱ የሚገቡ ዕርምጃዎች፣ የሥርዓተ-ፆታና አካል ጉዳተኛ አካታችነት፣ የጊዜ ሠሌዳና የሥራ ሰዓት፣ የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዎች ሥነ-ምግባር፣ የምርጫ አስተዳደርና ሚና፣ የእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የሥራ መደብ ኃላፊነቶች፣ የምርጫ ታዛቢዎችና ወኪሎች እንዲሁም የብዙኃን መገናኛ ኃላፊነትና ሚና፣ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ/የምዝገባ ኪት፣ ለመራጮች መረጃ ስለሚሰጥባቸው ፖስተሮች፣ ከመራጮች ምዝገባ ቀን በፊት ስለሚከናወኑ ተግባራት፣ የምዝገባ ሂደት ቅደም ተከተሎች፣ የምርጫ ጣቢያ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ስለሚቋቋምበት ሂደት፣ የልዩ ምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ ሂደት፣ ምርጫ ክልል ሪፖርት አቀራረብ፣ የመራጮች ምዝገባ ሂደት የደኅንነት ሕጎች፣ የምርጫ ቅሬታ አፈታቶች፣ ሎጀስቲክ፣ ኦፕሬሽንና አስተዳደራዊ የሆኑ ጉዳዮች ሥልጠናው ውስጥ ከተካተቱት አጀንዳዎች ውስጥ ይገኙበታል።
ቦርዱ ቀደም ሲል ነሐሴ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ቀደም በአሰልጣኝነት ለተሳተፉ የአንድ ቀን የክለሳ ሥልጠና በመስጠት ለሐረሪ ክልል፣ ለሶማሌ ክልል እና ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የመራጮች ምዝገባ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠናውን እንዲያከናውኑ አድርጓል። ለስልጠና ከሚውሉ ቁሳቁሶች በተጨማሪ ለመራጮች ምዝገባ የሚውሉ ቁሳቁሶች ሥርጭትም እንዲሁ ከማዕከል ወደ ምርጫ ክልሎች ነሐሴ 18-21 ቀን 2013 ዓ.ም. ተከናውኗል።