የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሀገር ዐቀፍ ምርጫውን አስመልክቶ በማስተማር ላይ ከተሠማሩ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሔሴ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ሀገር ዐቀፍ ምርጫውን አስመልክቶ በማስተማር ላይ ከተሠማሩ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት አካሄደ። የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ፣ የቦርድ አመራር አባል የሆኑት አበራ ደገፋ (ዶ/ር) እና ብዙወርቅ ከተተ፣ እንዲሁም የቦርዱ ፅ/ቤት ሃላፊ ሜላትወርቅ ኃይሉ የተገኙበትን መድረክ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ባደረጉት ንግግር የተከፈተ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ማኅበራቱ ለምርጫው ስኬታማነት የነበራቸውን ጉልህ አስተዋጽዖ ጠቅሰው አመስግነዋል።
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢን ንግግር ተከትሎም፤ የቦርድ አመራር አባል የሆኑት አበራ ደገፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለማኅበራቱ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ የማኅበራቱ ድርሻ የመራጮች ትምህርት ላይ ተሠማርተው አገልግሎታቸውን ከመስጠት ባሻገር በድኅረ-ምርጫውም በአገልግሎት ጊዜያቸው የነበራቸውን ሚና፤ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶችና ለመጪውስ ምን ይጠበቃል የሚለውን ሊያካትት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የቦርድ አመራሮቹን የመክፈቻ ንግግር በማስከተል በሲቪክና የመራጮች ትምህርት ክፍል አስተባባሪነት ማኅበራቱ በቡድን በቡድን ሆነው በምርጫው ወቅት አሳካናቸው ስለሚሏቸው፣ ተግዳሮቶች ነበሩ ስለሚሏቸውና በቀጣይ ምን መሠራት አለበት ስለሚሉት ነገር እንዲወያዩ ተደርጓል። ማኅበራቱ በቡድን ሆነው ባካሄዱት ውይይት የደረሱበትን ዝርዝር ነጥቦች በቡድን ተወካዮቻቸው አማካኝነት ያቀረቡ ሲሆን፤ ለመራጮች ትምህርት የተጠቀሟቸውን የማስተማሪያ አማራጮችና ቋንቋዎች በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን፤ የምርጫው ሰላማዊነት፣ የመራጮች በነቂስ ወጥተው መምረጣቸው፣ ትምህርቱ በብሬልና በኦዲዮ መታገዙ እንደ ስኬት ከተወሰዱ ነጥቦች መካክል ሲጠቀሱ፤ የፀጥታ ሁኔታ፣ ሎጀስቲክና ፋይናንስ ውሥንነት ከፈጠሩባቸው ዝርዝሮች ውስጥ ተጠቅሰዋል። በቀጣይ ምን ቢሠራ ይበጃል ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ የምርጫ ትምህርት በትምህርት ፖሊሲ ውስጥ ቢካተት የማኅበራቱን ሥራ እንደሚያቀልና የምርጫውን ስኬታማነትም ይበልጥ እንደሚያሳድገው በቡድን ተወካዮቹ አጽንዖት ተሰጥቷው ከተዘረዘሩት ውስጥ ይጠቀሳል። የቦርዱ የሥራ ክፍሎችም እንዲሁ በቡድን ተወያይተው ያጋጠሟቸውን ዝርዝር ነጥቦች አሰምተዋል።
የቦርድ አመራር አባል የሆኑት አበራ ደገፋ (ዶ/ር) በመድረኩ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ምርጫ የሁሉም ብቁ ዜጋ ሥራና ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸው፤ በምርጫ ትምህርት ጊዜ የሚሰጠው ትምህርት በተለይም የድምፅ መስጫ ወረቀት አጠቃቀምን አስመልክቶ የሚሰጠው ትምህርት ወሣኝ እንደሆነና የተበላሹ ድምፅ መስጫዎችን በማስቀረት የዜጎች ድምፅ እንዳይባክን እንደሚረዳ ገልጸዋል። በዕቅድ አፈጻጸም ወቅትም የትኞቹን ማስቀደምና የትኞቹን ደግሞ ማዘግየት እንደሚቻል ለይቶ ወደ ሥራ መግባቱ አፈጻጸሙን የተሻለ እንደሚያደገው፣ ሪፖርቶችንም በጊዜ ለቦርዱ ማስገባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል። በማኅበራቱ የተጠቀሱትን ተጨባጭነት ያላቸውን ውሥንነቶችም ቦርዱ እንደሚሠራባቸው፤ ያም ሲባል ግን ሁሉም ችግሮች በአንዴ ይፈታሉ ማለት እንዳይደለ አጽንዖት ሰጥተዋል። ቦርዱ ቀደም ሲል ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ሀገር ዐቀፍ ምርጫውን አስመልክቶ ቀዳሚ መግለጫ ካወጡና በመታዘብ ላይ ከተሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል።