Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ ባልተደረገባቸው ምርጫ ክልሎች ከሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት በማድረግ ቀጣዩን የድምፅ መስጫ ቀን ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ምርጫ ባልተደረገባቸው የምርጫ ክልሎች ከሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አደርጓል። ሁሉም የቦርዱ አመራሮች የተገኙበትን የምክክር መድረክ በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አማካኝነት ቦርዱ ሲሰራቸው የቆያቸው ስራዎች ሪፓርት ለፓርቲዎች ቀርቧል። በማስከተልም ምርጫ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች የሚኖረውን ቀጣይ የምርጫ ሂደት ከአካባቢዎቹ አጠቃላይ ሰላምና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ዝርዝር መረጃ የተሰጠ ሲሆን፤በቦርዱ ግምገማም ምርጫ ለማድረግ አመቺ ሁኔታ ያለባቸው ቦታዎችም ተለይተው ቀርበዋል። ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ከግንዛቤ በመክተት ቀጣዩ የድምፅ መስጫ ቀንን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን እንዲሰጡ ተጠይቋል።

ቦርዱ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ከግንዛቤ አስገብቶ ከፓርቲዎቹ ጋር ለመምከር ማሰቡን ተሣታፊዎቹ አድንቀው፣ በአስተያየታቸውም፤ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር ምርጫ ማድረጉ ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየት የሰጡ ሲኖሩ፤ በአንጻሩ ደግሞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የተደረገውም ምርጫ የተደረገው በተመሳሳይ የፀጥታ ችግር በነበረበት ሁኔታ፤ አንጻራዊ ሰላም ያለባቸው አካባቢዎች ተለይተው እንደተካሄደ ጠቅሰው፤ አሁን የሚካሄደው ምርጫም እንደቀደመው ሁሉ የተሻለ ፀጥታ ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት ማካሄድ እንደሚቻል አስተያየት ተሰጥቷል፣ በተጨማሪም ቀኑ ለመስቀል በአል የቀረበ ቀን በመሆኑ ማሻሻያ እንዲደረግበት ግብአታቸውን ሰጥተዋል። በመጨረሻም ቦርዱ የሚከተሉትን ውሳኔዎች የወሰነ ሲሆን ዝርዝር የምርጫው የጊዜ ሰሌዳም አብሮ ተያይዟል።

1. ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ ባልተካሄደባቸው ምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ቀን መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲሆን ወስኗል።

2. ድምፅ አሰጣጡ የሚከናወነው በሶማሌ ክልል፣ በሐረሪ ክልል እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የሚሆን ሲሆን የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህዝበ ውሳኔም በተመሳሳይ ቀን መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም የሚከናወን ይሆናል።

በቀሪ የምርጫ ክልሎች ላይ የሚኖረውን ሂደት አስመልክቶ ቦርዱ ተጨማሪ መረጃዎችን ይሰጣል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ነሐሴ 17 ቀን 2013 ዓ.ም

Share this post