Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ባልተደረገቸው እና በተቋረጠባቸው ምርጫ ክልሎችን አስመልክቶ ውሳኔ አስተላለፈ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫን በዋናነት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ያስፈጸመ ሲሆን በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ በታዪ ጉልህ ግድፈቶች፣ በመራጮች ምዝገባ ላይ በቀረቡ አቤቱታዎችን ለማጣራት ጊዜ በማስፈለጉ እንዲሁም ከጸጥታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የተነሳ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድምፅ አሰጣጥ ያልተደረገባቸው ቦታዎች እንዳሉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ ቀሪ ምርጫ ያልተከናወነባቸው የምርጫ ክልሎችን፣ የምርጫው ሂደት ያለበትን ሁኔታ እና የመሳሰሉትን በመገምገም የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።

የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመራጮች ምዝገባ

በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት ከፓለቲካ ፓርቲዎች በቀረበ አቤቱታ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ መጣራት ይገባዋል ብሎ በማመኑ የመራጮች ምዝገባ እንዲቆም በማድረግ 10 የምርጫ ክልሎች ላይ የመራጮች ምርመራን የሚመረምር ከተለያዩ ሲቪል ማህበራት የተወጣጣ አጣሪ ቡድን በመላክ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ ቀረቡትን አቤቲታዎች አጣርቷል። በማጣራት ሂደቱም አቤቱታ የቀረባበቸው ምርጫ ክልሎች ላይ የፓለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችን ምስክርነት በመስማት፣ የሰነድ ማስረጃዎችን በመመርመር፣ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱን ራሱን በየጣቢያዎች በመጎብኘት የማጣራት ሂደቱን ሪፓርት እና የውሳኔ ሃሳቡን ለቦርዱ እንዲሁም ለፓለቲካ ፓርቲዎች አቅርቧል። በዚህም መሰረት ቦርዱ ሪፓርቱን በመመርመር፣ ፓርቲዎች በሪፓርቱ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በመስማት የመርማሪ ቡድኑን ግኝት ሪፓርቶች በቃል በመስማት የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።

ምርመራ ከተደረገባቸው የምርጫ ክልሎች መካከል

1. የአጣሪ ቡድኑ ግኝትን መሰረት በማድረግ በሚከተሉት የምርጫ ክልሎች ላይ የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በድጋሚ እንዲከናወን ወስኗል። ሙሉ ለሙሉ የመራጮች ምዝገባ የሚደገምባቸው ቦታዎች፣

የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች

  • ጅጅጋ 1 ምርጫ ክልል
  • ጅጅጋ 2 ምርጫ ክልል

የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች

  • ቀብሪደሃር ከተማ ምርጫ ክልል
  • ቀብሪደሃር ወረዳ ምርጫ ክልል
  • መኢሶ ምርጫ ክልል
  • አፍደም ምርጫ ክልል

የመራጮች ምዝገባ የሚደገምባቸው በተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች

  • ዋርዴር ምርጫ ክልል ውስጥ አዶ ቀበሌ - 1 ምርጫ ጣቢያ እና ኤልድብር ቀበሌ - 2 ምርጫ ጣቢያዎች
  • ፊቅ ምርጫ ክልል -01 ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ 01 – 1 ምርጫ ጣቢያ
  • ገላዴን ምርጫ ክልል - 1 ምርጫ ጣቢያ
  • ጎዴ ከተማ ምርጫ ክልል - 4 ምርጫ ጣቢያዎች
  • ምስራቅ ኢሜ ምርጫ ክልል- 3 ምርጫ ጣቢያዎች
  • ቤራኖ ምርጫ ክልል - 3 ምርጫ ጣቢያ

2. በቀሩት የመራጮች ምዝገባ አቤቱታ የተነሳ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ የመራጮች ምዝገባ ቀናት ከመጠናቀቃቸው በፊት በመቋረጡ፣ የመራጮች ምዝገባ በተቋረጠባቸው ቦታዎች ሁሉ ለ5 ቀናት ያህል የመራጮች ምዝገባ ተሟልቶ እንዲጠናቀቅ ተወስኗል።

በሐረሪ ክልላዊ መንግስት የመራጮች ምዝገባ

በሐረሪ ክልላዊ መንግስት የመራጮች ምዝገባ ቦርዱ በሰጠው የአመዘጋገብ አሰራረር መሰረት ባለመከናወኑ ተቋርጦ ቦርዱ በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት እንደሚከናወን መገለጹ ይታወሳል። በዚህም መሰረት ቦርዱ በሃረሪ የተከናወነውን የመራጮች ምዝገባ ከመረመረ በኋላ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል።

  1. በጀጎል ዙሪያ እና ሁንደኔ የምርጫ ክልል ምዝገባው በተለያየ የክልል እና የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች የሚመርጡትን የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆችን እና ከብሔረሰቡ ውጪ ያሉ ተወላጆች ተቀላቅለው በመመዝገባቸው ምዝገባው ተለያይቶ እንደአዲስ ምዝገባ እንዲካሄድ ወስኗል።
  2. በጀጎል ልዩ ምርጫ ክልል የመራጮች ምዝገባ ተቋርጦ ስለነበር ለ5 ተጨማሪ ቀናት የማሟያ ምዝገባ እንዲከናወን ተወስኗል።
  3. በሰበር ችሎት በተወሰነው መሰረት ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች የሚመርጡባቸው ምርጫ ጣቢያዎች በሚከተሉት ቦታዎች የሚቋቋሙ ይሆናል።
  • አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር
  • ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ( አዳማ፣ ጭሮ፣ ኮምቦልቻ፣ ጉርሱም፣ ፈዲስ፣ ደደር እና ሃሮማያ)
  • ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር
  • ሶማሌ ብሔራዊ ክልል
  • ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ያለአግባብ ምዝገባ የተከናወነባቸው የምርጫ ክልሎች የድጋሚ ምርጫ ሙሉ ለሙሉ እንዲከናወን ወስኗል። እነሱም

  • ዘልማም ምርጫ ክልል
  • ዲዚ ልዩ ምርጫ ክልል
  • ሱርማ ምርጫ ክልል
  • ሙርሲ ምርጫ ክልል
  • ማጀት መደበኛ ምርጫ ክልል (ከልዩ ምርጫ ክልሎች ውጪ ያሉት ነዋሪዎች የሚመዘገቡበት) ናቸው። በደ/ብ/ብ/ህ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ የሚገኙ በቴፒ እና ሸኮ ልዩ የሚጠቃለሉ ጣቢያዎችን በተመለከተ ቦርዱ ተጨማሪ ውሳኔን የሚያስተላልፍ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ነሐሴ 17 ቀን 2013 ዓ.ም.

Share this post