Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተካሄደውን የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ በባለሞያዎች አጣሪ ቡድን አማካኝነት ያካሄደውን የምርመራ ሪፓርት ለፖለቲካ ፓርቲዎች አቀረበ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተካሄደውን የመራጮች ምዝግባን አስመልክቶ በባለሞያዎች የተካሄደውን ምርመራ ለፓርቲዎች እንዲቀርብ አድርጓል። የቦርዱ ሁሉም አመራሮች የተገኙበትን የምክክር መድረክ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ባደረጉት ንግግር የተከፈተ ሲሆን፤ የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎም በምክትል ሰብሳቢው ውብሸት አየለ አወያይነት በምርምራ ላይ ከተሠማሩት ዘጠኝ ቡድኖች ተወካዮች ቀርበው በየምርጫ ክልሎቹ ያደረጉትን ምርመራ ሂደት፣ ውጤት እና ለቦርዱ የሚያቀርቡትን የውሳኔ ሃሳብ አስረድተዋል። በምርመራ ሂደቱም በቀረቡት ቅሬታዎች ላይ ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው ግለሰቦች ጋር ባደረጓቸው ቃለመጠይቆች፣ በመሥክ ጉብኝት፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ በሰበሰቧቸው መረጃዎች፣ ከፎቶና ከተንቀሳቃሽ ምስል እንዲሁም ከቀረቡ ከተለያዩ የሠነድ ማስረጃዎችን በመጠቀም ያጠናቀሩትን ሪፖርት አቅርበዋል።

የአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት ከተሰማ በኋላ ቅሬታ ያቀረቡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሃሳብ እንዲሰጡ የተደረጉ ሲሆን፤ ፓርቲዎች ቅሬታዎቻቸውን፣ እና ከቦርዱ የሚጠብቁትን የውሳኔ አይነት በተመለከተ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፣ በጥያቄዎቻቸው መሰረት ቦርዱ የአጣሪ ቡድኑን ሪፓርት ለፓርቲዎች መቅረቡን ተከትሎ ውሳኔዎቹን ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች እንደሚያሳውቅ በምክትል ሰብሳቢው አማካኝነት ተገልጿል።

 

Share this post