Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የሚከተሉትን ዋና ዋና ውሳኔዎች አሳልፏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 02 ቀን 2013 ዓ.ም ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ካከናወነ በኋላ ባደረገው ስብሰባ ከ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ጋር የተያያዙ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።

1. 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን አስቀድሞ እንደተገለጸው በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በእለቱ ድምጽ መስጠት የማይቻልባቸው አካባቢዎች ድምጽ አሰጣጥ ጷግሜ 01 ቀን 2013 ዓ.ም ይከናወናል።

እነዚህም

  • ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል - መተከል፣ ሺናሻ ልዩ፣ ካማሽ እና ዳለቲ
  • በኦሮሚያ ክልል -ቤጊ፣ ሰኞ ገበያ፣ አያና፣ገሊላ፣አሊቦ፣ጊዳሚ፣ ኮምቦልቻ
  • አማራ ክልል-ማጀቴ (ማኮይ)፣ አርጎባ ልዩ፣ ሸዋሮቢት፣ ኤፌሶን፣ ጭልጋ 1፣ ጭልጋ 2፣ ላይ አርማጭ፣ አንኮበር
  • ደ/ብ/ብ/ህ ክልል - ሱርማ ልዩ ፣ ዲዚ ልዩ፣ ቀይ አፈር መደበኛ፣ ማጀት መደበኛ፣ ሸኮ ልዩ፣ ቴፒ
  • ሐረሪ ክልል - ጀጎል ልዩ ፣ ጀጎል መደበኛ ናቸው።

በፀጥታ ችግሮች የተነሳ ድምጽ አሰጣጥ በዚህ ቀን በሚከናውንበት ወቅት የጸጥታው ሁኔታ የማሻሻል ሃላፊነት ያለባቸው የመንግስት ፀጥታ አካላት ለዚሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ ቦርዱ በዚህ አጋጣሚ ለማሳወቅ ይወዳል።

2. ቦርዱ 54 የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ችግሮች ያጋጠሙ መሆናቸውን ገልጾ ከፓርቲዎች ጋር ምክክር በማድረግ አማራጭ መፍትሄዎች ላይ ሲወያይ እንደነበር ይታወሳል። ከነዚህም የምርጫ ክልሎች መካከል በፍጥነት ህትመት ሊከናወንባቸው የሚችልባቸውን መንገዶች በመፈለግ የድምጽ መስጫ ወረቀት ችግር ያለባቸው የምርጫ ክልሎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 27 ሆኗል። በዚህም መሰረት በነዚህ 27 የክልል እና የተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ድምጽ የሚሰጠው ከላይ በተጠቀሰው ጷግሜ 01 ቀን 2013 ዓ.ም ይሆናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምጽ መስጫ ወረቀትን ለማጓጓዝ ከፍተኛ እና ልዩ ትብብር እያደረገ ላለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡

3. በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ በ14 ምርጫ ክልሎች ምርመራ ተከናውኖ መጠናቀቁ ይታወሳል። ከዚህም በተጨማሪ የድምጽ መስጫ ወረቀት ድጋሚ ህትመት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚነካቸው ክልሎች አንዱ ሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኙ ምርጫ ክልሎች በመሆናቸው ቦርዱ በክልሉ የሚደረገው ድምጽ አሰጣጥ በጷግሜ 01 ቀን 2013 እንዲደረግ ወስኗል። ከዚያ በፊት ከመራጮች ምዝገባ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን በምርመራው ውጤት መሰረት የሚያጠናቅቅ እና ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።

4. የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ከአጠቃላይ ምርጫው ጋር ሰኔ 14 ቀን ይካሄዳል ተብሎ ታቅዶ የቆየ ቢሆንም ህዝበ ውሳኔው በሚከናውንባቸው ምርጫ ክልሎች በጸጥታ ችግር የተነሳ ድምጽ የማይሰጥባቸው ምርጫ ክልሎች በመኖራቸው የህዝበ ውሳኔውን ምእሉነት ስለሚያጎድለው እና የሁሉንም መራጮች ምርጫ በትክክል መመዘን ስለማይቻል.፣ ህዝበ ውሳኔው ከሌሎች የምርጫ ክልሎች ጋር ጷግሜ 01 ቀን 2013 ዓ.ም የሚከናወን ይሆናል።

5. የመራጮች ምዝገባን የተረጋገጠ ቁጥር ማጣራት ሂደቱን ያጠናቀቀ ሲሆን በዚህም መሰረት ለ6ተኛው አገራዊ ምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 37.4 ሚልዮን ሆኗል። ይህ ቁጥር በሶማሌ ክልል በምርመራ የተነሳ የመራጮች ምዝገባ የታገደባቸው 14 ምርጫ ክልሎችን አይጨምርም። ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከቦርዱ እውቀውና ውጪ የተከፈቱ 2፣ በድሬደዋ ከተማ መስተዳድር ከቦርዱ እውቅና ውጪ የተከፈቱ 6 እንዲሁም በደ/ብ/ብ/ህ ክልል ከቦርዱ እውቅና ውጪ የተከፈቱ 71 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተደረጉ የመራጮች ምዝገባዎች ህጋዊ አይደሉም ሲል ቦርዱ ወስኗል። የተመዘገቡ መራጮችን ድምፅ አሰጣጥ ሂደት አስመልክቶ ቦርዱ ከድምጽ አሰጣጥ ቀን በፊት ውሳኔ የሚሰጥ ይሆናል።

በድምጽ መስጫ ወረቀት ድጋሚ ህትመት ችግር የተነሳ ድምጽ አሰጣጥ ሂደታቸው ወደ ጷግሜ 01 የተዘዋወሩ የምርጫ ክልሎች ዝርዝር ከስር የሚገኝ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ ያጋጠመውን ችግር አስመልክቶ የማጣራት እና የምርመራ ስራ አከናውኖ ውጤቱን የሚያሳውቅ ይሆናል።

የምርጫ ካርድ የወሰዱ (የተሻሻለ)

የድምጽ መስጫ ወረቀቶች በድጋሚ ህትመት የሚስፈልጋቸዉ የምርጫ ክልሎች ወደ መስከረም የተሻገሩ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

Share this post