የመራጮች ምዝገባ ሒደት ያልተጀመረባቸው የምርጫ ክልሎችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መረጃ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን እያከናወነ እንደሆነ በምዝገባ ሂደቱም ወቅት የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል። እንደሚታወቀው የመራጮች ምዝገባ በተወሰኑ ምርጫ ክልሎች መዘግየቱ የሚታወስ ነው። ቦርዱ ከክልል መስተዳድር አካላት ጋር ባደረገው ከፍተኛ የትብብር ስራ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው ቦታዎች የመራጮች ምዝገባን ለማስጀመር ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በዚህም መሰረት የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 29 - ግንቦት 13 ቀን 2013 ድረስ በልዩ ሁኔታ እንዲከናወን ወስኗል።
ከነዚህም መሰረት
• በምእራብ ወለጋ ዞን (ለቤጊ እና ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል ውጨ)
• በምስራቅ ወለጋ ዞን (ከአያና እና ገሊላ ምርጫ ክልል ውጪ)
• በቄለም ወለጋ ዞን
• በሆሮ ጉድሩ ዞን (ከአሊቦ፣ ጊዳም እና ኮምቦልቻ ምርጫ ክልል ውጪ) ከሚገኙት 31 ምርጫ ክልሎች መካከል በ24ቱ ላይ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በከማሽ ዞን ከሚገኙት አምስት የምርጫ ክልሎች በአራቱ የመራጮች ምዝገባ (ከሴዳል ምርጫ ክልል ውጪ) ከላይ በተጠቀሱት ቀናት እንዲከናወን ወስኗል።
ከዚህም በተጨማሪ የመራጮች ምዝገባ በጸጥታ ችግር የተነሳ ሳይከናወንበት የነበረው የአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔር ልዪ ዞን የሚገኙት ዳዋ ጨፌ፣ ጨፋ ሮቢት እና ባቲ ምርጫ ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 29 - ግንቦት 13 ቀን 2013 ድረስ ይከናወናል።
በመሆኑም ፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያ እና ሲቪል ማህበራት የመራጮች ምዝገባን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን መረጃን በመስጠት እና አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ በማድረግ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ