መረጃ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በክስ ሂደት ላያ ያሉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች
- የካ ክፍለከተማ
- ኮልፉ ቀራኒዮ ክፍለከተማ
- ንፋስ ስልክ ላፍቶ
እንዲሁም የተወካዮች ምክር ቤት
ምርጫ ክልል 26 እና 27 በእጩነት ለመወዳደር ጥያቄ አቅርበው እንዳልተቀበለው ይታወቃል።
በዚህም መሰረት መጀመሪያ የምርጫ ክልሎቹ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ፣ በማስከተል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ቀጥሎ ከፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእጩነት ምዝገባ ጥያቄው አግባብ አይደለም ብሎ ሲከራከር እንደነበር ይታወሳል። በዚህም መሰረት ከፍተኛው ፍርድ ቤትም የቦርዱን አሰራር አጽድቆ ነበር።
ክርክሩ በይግባኝ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ 2ተኛ ችሎት ቀርቦ ሰበር ሰሚው ችሎት እጩዎች መመዝገብ መብት አላቸው ብሎ ወስኗል። ውሳኔው እጅግ በጣም ዘግይቶ ምርጫው ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊከናወን መሆኑ ለአፈጻጸምም ሆነ በጊዜው ማነስ የተነሳ ተጨማሪ የህግ ክልከላዎችን ማምጣቱን በማንሳት ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ በአፈጻጸም ደረጃ ግን ማብራሪያን የሚጠይቅ አቤቱታ ለሰበር ሰሚ ችሎቱም ከማስገባቱ በላይ የቦርዱ ሰብሳቢ ለሰበር ሰሚ ችሎቱ ቀርበው የአፈጻጸም ትእዛዝ እንዲሰጥላቸው አቤቱታቸውን በግንባር አቅርበዋል። ይህም ሆኖ ከሰበር ሰሚ ችሎቱ በኩል ውሳኔው አፈጻጸም ላይ ተጨማሪ ትእዛዝ እንደማይሰጥ እና በአፈጻጸም እንደሚታይ የተገለጸ ሲሆን ፓርቲው በቦርዱ ላይ የአፈጻጸም ፋይል ከፍቷል።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከፈተው የአፈጻጸም ችሎቱ ላይ የተገኙት የቦርዱ ሰብሳቢ ቦርዱ የሄደበትን ሂደት አብራርተው ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው የሂደቱን አስቸጋሪነት ማስረዳታቸውን እና በመጨረሻም ቦርዱ ውሳኔውን ማስፈጸም መጀመሩን አስረድተዋል።
የሰበር ሰሚ ችሎቱን ውሳኔ በማክበር እንዲሁም ካለው የጊዜ ጥበት አንጻር የህግ ክርክሩ ከዚህ በላይ ቢጓተት ከፍተኛ የሆነው የአዲስ አበባ የምርጫ ካርታ የሚስተጓጎልበት መሆኑን በመረዳት ቦርዱ 1.3 ሚልዩን የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን በማስወረድ አዲስ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን አሳትሟል፣ በዚህም የተነሳ ቦርዱ 3.5 ሚልዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ተዳርጓል።
የምርጫ ክርክሩ የተደረገባቸው ሶስቱ የከተማ መስተዳድር ክፍለከተሞች እና አንድ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የሚያካትቱት ምርጫ ክልል/ክፍለከተማ እና ምርጫ ጣቢያ የሚከተለው ሊንክ ላይ ይገኛል።