የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሎጀስቲክስ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አካሄደ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ዛሬ ሰኔ 02 ቀን 2013 ዓ.ም የምክክር መድረክ አከናውኗል። ይህ በተደጋጋሚ ከሚደረጉ የምክክር መድረኮች አንዱ የሆነው ከፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ምክክር በዋናነት ቦርዱ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመትን አስመልክቶ ያጋጠመውን ተግዳሮት ለፓርቲዎች ሪፓርት ያቀረበበት ነው።
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በሪፓርታቸው እንዳቀረቡት የእጩዎችን ቁጥር መሰረት አድርጎ በተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ወቅት ፓርቲዎች የእጩዎች ቁጥር ላይ ባቀረቡት አቤቱታ፣ በማስከተልም በድምጽ መስጫ ወረቀት እና በውጤት ማሳወቂያ ፎርሞች መካከል የማስታረቅ ስራ ሲሰራ የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ የተለያዩ ጉድለቶች መገኘታቸውን አሳውቀዋል። በዚህም መሰረት የቦርዱ ኦፕሬሽን ክፍል ባከናወነው ኦዲት 54 የምርጫ ክልሎች ድምጽ መስጫ ወረቀቶች ድጋሚ ህትመት የሚያስፈልጋቸው ሆነው ተገኝተዋል።
በክልል ሲታይም
- አፋር - 6 ምርጫ ክልል (1ዱ የተወካዮች ምክር ቤት)
- አማራ- 11 ምርጫ ክልል (3ቱ የተወካዮች ምክር ቤት)
- ቤኒሻንጉል ጉሙዝ - 2 ምርጫ ክልሎች ( የክልል ምክር ቤት)
- ጋምቤላ - 3 ምርጫ ክልሎች (የክልል ምክር ቤት)
- ኦሮሚያ - 2 ምርጫ ክልል (የክልል ምክር ቤት)
- ደ/ብ/ብ/ህ- 15 ምርጫ ክልሎች (1ዱ ለተወካዮች ምክር ቤት)
- ሶማሌ- 14 ( የክልል ምክር ቤት)
- ድሬዳዋ - 1 (የከተማ ምክር ቤት) ድጋሚ ህትመት የሚያስፈልጋቸው ምርጫ ክልሎች ያሏቸው ናቸው።
የቦርዱ ሰብሳቢ ለተፈጠረው ችግር በቦርዱ የተወሰዱ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን አቅርበው በነዚህ ምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን አትሞ ለማድረስ የሚኖረውን ችግር በማንሳት እና በአጠቃላይ የሚያመጣውን የእሸጋ እና የስርጭት ተጽእኖ ካብራሩ በኋላ በነዚህ የምርጫ ክልሎች ድምጽ መስጫ ወረቀቶችን በድምጽ መስጫው ቀን ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት አስመልክቶ ፓርቲዎች ሃሳብ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ፓርቲዎች በስራ ላይ እንዲህ አይነት ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ገልጸው የድጋሚ ህትመቱ በአገር ውስጥ የሚከነወንበት እድል ቢታይ፣ አንዳንድ የምርጫ ክልሎች ደሞ ለጸጥታ የተነሳ ችግር ያጋጠመባቸው ቦታዎች ድምጽ በሚሰጡበት ወቅት አብረው የሚሰጡበት እድል መኖሩን እንደሌላ አማራጭ አቅርበዋል።
በዚህም መሰረት ቦርዱ ይህንን ችግር ለመፍታት ያሉትን ሁለት አማራጮች መሆናቸውን አንደኛው አማራጭ የድምፅ መስጫ ወረቀቱን አገር ውስጥ ህትመት ማከናወን ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ደሞ ከላይ የተጠቀሱትን ምርጫ ክልሎች በጸጥታ ችግር የተነሳ ሰኔ 14 ቀን ድምጽ ከማይሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች ጋር በጋራ ማከናውን መሆኑን ጠቅሶ በሌሎች ምርጫ ክልሎች ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በተወሰነለት ቀን ሰኔ 14 ቀን የሚከናወን መሆኑን ተጨማሪ መረጃዎቸን ለፓርቲዎች እና ለመራጮች እንደሚሰጥም አሳውቋል።