የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የእጩዎች ምዝገባን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። የእጬዎች ምዝገባ ሂደቱን በመገምገም እንዲሁም ከፓለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በማገናዘብ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትም እየሰራ ነው። በመሆኑም በአዋጅ 1162/2011 እንዲሁም በእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16(1) መሰረት የመንግስት ሰራተኛ እጩዎች ስራቸውን መልቀቅ ሳያስፈልጋቸው በእጩነት ለመወዳደር እንደሚችሉ ይደነግጋል። እንዲሁም እጩ ከሆኑ በኃላ በምርጫ ወቅት ያለደምወዝ ፈቃድ የማግኘት መብታቸውም በህግ የተሰጠ ነው።

ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባን በሚያከናውንበት ወቅት በእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16(2) ትርጉም ተዛብቶ በመወሰዱ የተለያዩ የምርጫ ክልሎች የመንግስት ሰራተኛ እጩዎችን ያለደምወዝ ፈቃድ የተወሰደበትን ሰነድ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን ተረድቷል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የተፈጠረውን መምታታት ለመፍታት እጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16 (2) እንዲሰረዝ የወሰነ ሲሆን ይህንን ተከትሎ ማንኛውም እጩ ለመመዝገብ ያለደምወዝ ፍቃድ የማያስፈልገው መሆኑን አጽንኦት በመስጠት የዚህን የአሰራር ክፍተት ለመድፈን ለምርጫ ክልል /ቤት አስፈጻሚዎች ይኸው መልእክት እንዲተላለፍ የሚደረግ መሆኑን ቦርዱ ያሳውቃል።