Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ነክ ግጭት መከላከል የጋራ መድረክ አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዚያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. የአዲስ አበባ የምርጫ ነክ ግጭቶች መከላከል የጋራ መድረክ አካሄደ። የመከላከያ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የከተማ መስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት፣ የሴቶች ፌደሬሽን፣ አካል ጉዳተኞች ማኅበር፣ የሃይማኖቶች ጉባዔ፣ ሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶቸ ኮሚሽን ተወካዮች የተጋበዙበትን መድርክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ የምርጫው ሰላማዊ መሆን ሙሉ በሙሉ ለፀጥታ ኃይሉ የሚተው እንዳይሆን፤ እንዲሁም ምርጫ በባህሪው የብዙ ባለድርሻ አካላትን የሚያሣትፍ በመሆኑ መድረኩን ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል። ምክትል ሰብሳቢ አክለውም የጋራ መድረኩ ከምርጫ ጋር በተገናኘ የሚያጋጥሙ ግጭቶችን ከወዲሁ በመለየት በቀላሉና በፍጥነት ለመፍታት እንደሚያስችል ያላቸውን ዕምንት ገልጸዋል።

የምክትል ሰብሳቢውን ንግግር ተከትሎ በቦርዱ ምርጫ ነክ ግጭቶች አስቀድሞ መከላከል ክፍል ባልደረባ አማካኝነት የምርጫ ነክ ግጭቶች ዓይነትና መንስዔዎች፣ በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ የጋራ መድረኩ ሊኖረው የሚገባው መዋቅራዊ አደረጃጀትና የሥራ ኃላፊነት በዝርዝር የቀረቡ ሲሆን፤ ከተሣታፊዎች በዝርዝር ማብራሪያው ላይ ጥያቄዎችና ተጨማሪ ገንቢ ሃሳቦች ተሰብስቧል። ለቀረቡት ጥያቄዎች በምክትል ሰብሳቢውና በቦርዱ ምርጫ ነክ ግጭቶች አስቀድሞ መከላከል ክፍል ባልደረባ አማካኝነት መልስ ተሰጥቶባቸው መድረኩ ተጠናቋል። መድረኩ የመጀመሪያና የትውውቅ የነበረ ሲሆን፤ በቀጣይም በጉዳዩ ላይ ሥልጠናና ተጨማሪ መድረኮች የሚኖሩ ይሆናል።

Share this post