Skip to main content

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባን አስመልክቶ የተሰጠ መረጃ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀበት ጊዜ ጀምሮ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በመቀበል፣ ችግሮችን በመፍታት እንዲሁም የድምጽ መስጫ ወረቀት ቅደም ተከተል ሎተሪን በማከናወን የእጩዎችን ዝርዝር አጠናቆ ለድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ሲያዘጋጅ ቆይቷል።

በምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 39 (3) የፖለቲካ ፓርቲ እጩውን መለወጥ ወይም መተካት የሚቻልበት ቀን የእጩ ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ካለቀ በኋላ ከሆነ ከድምጽ መስጫው ቀን ከአንድ ወር በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል። በዚህም መሰረት ከዛሬ ከሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የእጩ መተካት፣ መቀየር፣ መለወጥ እና ማንኛውንም አይነት ማሻሻያ የማይቀበል መሆኑን ይገልጻል።

እስከአሁን የቀረቡ ከእጩዎች ለውጥ ጋር የተገናኙ ጥያቄዎች የሚስተናገዱ ሲሆን ከዚህ በኋላ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት እየተከናወነ በመሆኑ እና በህግ የተቀመጠውም ግዴታ በማብቃቱ ከእጩዎች ምዝገባ ጋር የተገናኘ ማንኛውንም አይነት አቤቱታ መቀበል ማቆሙን ፓርቲዎች ተረድተው ከዚህ በፊት ያስገቧቸው የለውጥ ጥያቄዎችን ብቻ እንዲከታተሉ እናስታውቃለን።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም

Share this post