Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ወረቀት የኅትመት ሂደትንና የደኅንነት አጠባበቅ ሥርዓቱን ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አስጎበኘ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓለቲካ ፓርቲዎች እና ሚዲያዎች የተወጣጣ የልኡካን ቡድን ወደደቡብ አፍሪካ በመላክ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመትን እንዲጎበኙ አደረገ። በቦርዱ ከፍተኛ አመራር ፍቅሬ ገብረ ሕይወት ለተመሩት ከፓርቲዎች እና ከሚዲያዎች ለተውጣጡ ተወካዮች የድምፅ መስጫ ወረቀት የኅትመት ሂደቱን፣ የቴክኒክና የደኅንነት አጠባበቅ ሥርዓቱን በዝርዝር ማሳየት ችሏል። ቦርዱ የፍትሐዊ አሠራሩ አንዱ ማሳያ አድርጎ ከሚወስደው የድምፅ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተል መወሠኛ ሎተሪን በይፋ ካስጀመረበት ከመጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመቱ የተጀመረ ሲሆን፤ ይህንንም ሥራ ከሚያካሂዱት ሁለት የኅትመት ድርጅቶች አንዱ በሆነውና በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን የሬን-ፎርም ኅትመት ማኅበር ከፓርቲዎች እና ከሚዲያዎች የተወጣጡ የታዛቢ ቡድኑ አባላት ጎብኝተውታል።

በጉብኝቱም የሥራ ሂደትና የኅትመቱ የደኅንነት አጠባበቁን ምን እንደሚመስል በኅትመት ኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ተሰጥቷል። ጎብኝዎች ግልፅ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉትን ነገር በሥራ ኃላፊዎቹና በቦርዱ አመራር ፍቅሬ ገብረ ሕይወት አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቷቸው የኅትመት ሂደቱ ምን እንደሚመስል፤ ከጥሬ ማቴሪያል ምርት አንሥቶ እስከ ኅትመት ሂደቱና የማሸግ ሥርዓቱ ድረስ ያለውን አጠቃላይ ሂደት የተመለከተ ጉብኝት ተካሂዷል። ፓርቲዎቹም ከጉብኝቱ በኋላ ለብዙኃን መገናኛ አካላት በሰጡት አስተያየት፤ ባዩት ነገር መደሰታቸውን፤ ጉብኝቱም የቦርዱን ግልጽ አሠራር ማሳያ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፤ የጉብኝት አጋጣሚውም ፓርቲዎቹ ተቀራርበው ለመወያየት አጋጣሚን የፈጠረ እንደነበር ገልጸዋል።

በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው ኅትመት የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመቱን 45% የሚሸፍን ሲሆን፤ ይህውም የደ/ብ/ብ/ክ፣ የአማራ ክልል፤ የሲዳማ ክልልና የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሣኔን ያካትታል። ቀሪውና 55% የሚሸፍነው የኅትመት ሥራ ዱባይ በሚገኘው አል-ጉህራር ማኅበር እየተከናወነ ይገኛል። ለአራት ቀናት በቆየው ጉብኝትም የብልጽግና ፓርቲ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የህብር ኢትዮጵያ ተወካይ (ህብር)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው እና የሚዲያ አካላትም ተሳትፈዋል።

Share this post