Skip to main content

የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ በጀመረባቸው ምርጫ ክልሎች መራጮች ምዝገባ ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርደ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን በአጠቃላይ ያጠናቀቀ ቢሆንም ዘግይተው የጀመሩ ምርጫ ክልሎች ምዝገባ ሲከናወን እንደነበር ይታወቃል። በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ዘግይተው የጀመሩ ምርጫ ክልሎች ላይ ያለው የመራጮች ምዝገባ ትላንትና ተጠናቋል።

በዚህም መሰረት የመራጮች ምዝገባ በትላንትና ግንቦት 13 ቀን 2013 የተጠናቀቀባቸው ቦታዎች

  • በምእራብ ወለጋ ዞን ( ለቤጊ እና ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል ውጨ)
  • በምስራቅ ወለጋ ዞን ( ከአያና እና ገሊላ ምርጫ ክልል ውጪ)
  • በቄለም ወለጋ ዞን ( ጊዳም ምርጫ ክልል ውጪ)
  • በሆሮ ጉድሩ ዞን ( ከአሊቦ እና ኮምቦልቻ ምርጫ ክልል ውጪ) የሚገኙት 24 የምርጫ ክልሎች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን ሲከናወን የነበው ምዝገባ እና የአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔር ልዪ ዞን የሚገኙት ዳዋ ጨፌ፣ ጨፋ ሮቢት እና ባቲ ምርጫ ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ተጠናቋል።

በዚህም መሰረት በነዚህ ምርጫ ክልሎች የመራጮች መዝገብ ለሚቀጥሉት 10 ቀናት ማለትም እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ድረስ ለህዝብ ይፋ የሚሆን ሲሆን የመራጮች መዝገባ ቀን ከተጠናቀቀበት ቀን በኋላ ምንም አይነት ምዝገባ ማካሄድ አይቻልም። ሂደቱም ከዚህ በፊት በቦርዱ የተገለጸ ሲሆን የሚከተሉት ዋና ዋና ሂደቶች የመራጮችን መዝገብ ይፋ ማድረግ ውስጥ ይካተታሉ።

  • የመራጮችን መዝገብ ለመመልከት የምትቀርብ/የሚቀርብ ሰው የመራጭነት ምዝገባ ካርዷን/ካርዱን እና የማንነት መታወቂያ ካርድ ወይም ማንነቱዋን/ማንነቱን የሚያውቅ ምስክር ማቅረብ አለባት/አለበት::
  • የመራጮችን መዝገብ የምትመለከት/የሚመለከት ሰው በመዝገብ ሹሟ/ሹሙ አማካኝነት የምትፈልገው/የሚፈልገውን መረጃ ያለበትን ገጽ /ገፆች/ በዓይን ከማየት ወይም መረጃው ሲነበብላት/ሲነበብለት ከማዳመጥና ማስታወሻ ከመያዝ ውጪ በእጇ/በእጁ መንካት፣ መዝገቡ ላይ መፃፍ፣ ምልክት ማድረግ፣ ወይም ፎቶግራፍ ማንሳት የተከለከለ ነው::
  • የመራጮች መዝገብ ህዝብ በግልፅ እንዲያየው ሲደረግ የምርጫ ታዛቢዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የግል እጩ ወኪሎች እና የምርጫ አስፈፃሚዎች ሊገኙ ይችላሉ፡፡
  • እውቅና መታወቂያ ያላቸው የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የእውቅና መታወቂያ ያላቸው የሚዲያ ባለሞያዎች እና ታዛቢዎች ይፋ የሆነውን መዝገብ መመልከትም ሆነ ይፋ የማድረግ ሂደቱን መከታተል ይችላሉ።
  • በመራጭነት የተመዘገበች/የተመዘገበ ሰው የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ይፋ በሆነበት ጊዜ የግል መረጃዋን/መረጃውን በተመለከተ ስህተት አለ የሚል ቅሬታ ካላት/ካለው እንዲስተካከልላት/እንዲስተካከልለት ለምርጫ ጣቢያው ማመልከት ትችላለች/ይችላል፡፡ ምርጫ አስፈጻሚውም ሰነዶችን በማየት በህጉ መሰረት ማስተካከያ ያደርጋል።

Share this post