የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች ትምህርት ላይ ከተሠማሩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች ትምህርት ላይ ከተሠማሩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ። ውይይቱን የቦርዱ አመራር አበራ ደገፋ (ዶ/ር) በንግግር የከፈቱት ሲሆን፤ በንግግራቸውም ቦርዱ የመራጮች ትምህርት ለሚያስተምሩ 167 የሲቪክ ማኅበራት ፍቃድ የሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህም ፈቃድ የተሰጣቸው የሲቪክ ማኅበራት በሰጡት የመራጮች ትምህርት አማካኝነት ካርድ የወሰዱ ዜጎች ቁጥር መሻሻል ያሳየ መሆኑ፤ ለዚህም ከፍተኛ አክብሮት እንዳላቸው ተናግረዋል። ሲቪክ ማኅበራቱ በቀጣይ በሚከናወነው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ዜጎች በንቃት እንዲሣተፉና ድምፃቸውን በነፃነት ለፈለጉት ዕጩ እንዲሰጡ ማሰተማር አሰፈላጊ መሆኑን፤ በድምፅ አሰጣጥ ሂደት በመራጮች መሳሳት የሚባክን ድምፅ እንዳይኖር በመራጮች ትምህርት አሰጣጥ ላይ የተሰማሩ የሲቪክ ማህበራት ትምሀርቱን በደንብ መስጠት እንደሚኖርባቸው፤ እንዲሁም በድኅረ ምርጫ ሁኔታዎች ሰላማዊ እንዲሆን ዜጎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተገቢው ትምህርትና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
የቦርድ አመራሩን ንግግር ተከትሎ በቦርዱ የሲቪክና የመራጮች ትምህርት ክፍል ኃላፊዋ አመካኝነት የመድረኩን አስፈላጊነትና ከመድረኩ ምን እንደሚጠበቅ የተብራራ ሲሆን፤ ሌሎች የሲቪክና የመራጮች ትምህርት ክፍል ባልደረቦችም በበኩላቸው አጠቃላይ በመራጮች ትምህርት ላይ የተሠማሩ የሲቪክ ማኅበራትን እንቅስቃሴና ቁጥጥር ሪፖርት አቅርበው መድርኩ ለተሣታፊዎች ክፍት ሆኗል። ተሣታፊዎቹ በማስተማር ወቅት የፋይናንስ ውሥንነት የፈጠረባቸውን ዕክል፣ የአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታ ተግዳሮት እንደነበር፣ እንዲሁም ምንም እንኳን ከቦርዱ የተሰጣቸውን የዕውቅና ባጅና ደብዳቤ ቢያሳዩም የመንግሥት የፀጥታ አካላት በማስተማር ወቅት ከበላይ አካል አልተነገረንም በሚል ክልከላ እያደረጉባቸው በሥራቸው ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንደፈጠሩባቸው ገልጸዋል።
ከላይ የተጠቀሱትንና መሰል ጥያቄና አስተያየቶች በቦርዱ አመራር አበራ ደገፉ (ዶ/ር) እና በቦርዱ የሲቪክና የመራጮች ትምህርት ክፍል ኃላፊዋ አመካኝነት መልስ ተሰጥቶባቸዋል። አበራ (ዶ/ር) በንግግራቸው ማኅበራቱ የሚያሠማሯቸው አስተማሪዎችን ገለልተኛነት ከማረጋገጥ አንጻር በቂ ክትትል ማድርግ ያለውን አስፈላጊነት፣ መራጩ ኅብረተሰብ የድምፁን ዋጋ በአግባቡ እንዲረዳና የመራጭነት ካርዱም ከግለሰቡ ሊለይ እንደማይገባ፤ እንዲሁም በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የሚኖሩትን እያንዳንዱ ቅደም ተከተል በዝርዝር መራጩን ማሳወቅ ያለውን አስፈላጊነት አብራርተዋል። በድምፅ አሰጣት ሂደትም የድምፅ መስጫ ወረቀት በሚበላሽበት ጊዜ የሚኖረውን የአወጋገድ ሥርዓትም ጭምረው አብራርተዋል። የፀጥታ አካላትን ተባባሪነት አስመልክቶ ለተነሡ ጥያቄዎች በሰጡት መልስ፤ ቦርዱ ለሲቪክ ማኅበራቱ ሕጋዊነት የሰጠው የዕውቅ ሰርተፍኬት፣ ባጅ እንዲሁም ደብዳቤ በቂ መሆኑን ገልጸው፤ ማንኛውም የመንግሥት ተቋማት የመተባበር ግዴታ እንዳለባቸው በዐዋጁ ላይ የተቀመጠ በመሆኑ፤ የመራጮች ትምህርት በሚሰጥባቸው ቀሪ ጊዜያት የፀጥታ አካላትም ሆኑ የባለድርሻ አካላት ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው አብራርተዋል።