Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎች ምዝግባ እና ተያያዥ የምርጫ ሁነቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶችን ለፖለቲካ ፓርቲዎች አቀረበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. የ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ እና ተያያዥ የምርጫ ሁነቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶች ለፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙኃን በተገኙበት አቀረበ። ሪፖርቱ ሦስት አጀንዳዎችን መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ በቅድመ ምርጫ ጊዜ፣ በምርጫው ጊዜና በድኅረ-ምርጫ ጊዜ የሚኖረውን የመረጃ አሰጣጥ ሂደት የተመለከተ ሪፖርት በቦርዱ የመራጮች ትምህርት ክፍል ባልደረባ አማካኝነት ሲቀርብ፤ ቦርዱ የተለያዩ የምርጫ ክልሎች በሚከፍትበት ወቅት ያጋጠሙትን የኦፕሬሽን እና የሎጂስቲክ ፍሰትን የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች በቦርዱ የኦፕሬሽን ክፍል ባልደረባ ቀርቧል።

አጠቃላይ ሂደቱ ምን እንደሚመስልና ከባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል የሚለውን ደግሞ በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ቀርቧል። ሰብሳቢዋ በንግግራቸው በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን የሎጀስቲክ እንቅስቃሴና አስፈጻሚዎች በተገቢው ሰዓት ከምርጫ ጽ/ቤት ወደ ምርጫ ጽ/ቤት እየተንቀሳቀሱ ሥራቸውን ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመጓጓዟ መኪኖች ከክልል መንግሥት በሚፈለገው መጠን እንዳልቀረበና ይኽም አጠቃላይ የአፈጻጸም ሂደቱ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ሚና በመግለጽ፤ መንግሥትም ሆነ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚጠየቁትን ትብብር በተገቢው ሰዓት መፈጸማቸው አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ላይ እንዲሁም የጊዜ ሠሌዳውን ተከትሎ ከመሥራት አንጻር ትልቅ ትርጉም ስላለው ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል። የባለድርሻ አካላት ኃላፊነትን መወጣት ላይ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ሰብሳቢዋ፤ ምርጫው በቦርዱ ትከሻ ላይ እንደወደቀ አድርጎ መታሳብ እንድሌለበት ሊሠመርበት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተሠሩ ካሉት ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ ቦርዱን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ አንዱ ሲሆን፤ በዕጩዎች ምዝገባ ወቅት የነበረውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ያጋጠሙ ሁነቶችን የተመለከቱ ገለጻዎች በቦርዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ባልደረባ ቀርቧል። የቀረቡትን ሪፖርቶች ተከትሎ መድረኩ ለተሣታፊዎች ክፍት የተደረገ ሲሆን፤ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቦርዱ በጊዜ ሠሌዳው መሠረተ እየከወነ ያላቸው ተግባራት ላይ እንደየ ቅደም ተከተላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሃሳብና አስተያየት እየጠየቀ በማገናዘብ መሄዱን አበረታተው፤ በእጩዎች ምዝገባ ወቅት አጋጠሙን ያሉትን ዕክሎች በዝርዝር አቅርበዋል። በሁለት ዙር ለተሰበሰበው የተሣታፊዎች አስተያየት ዋና ሰብሳቢዋ መልስ የሰጡ ሲሆን፤ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ አጋጠመን ያሉትን እክሎች መግለጻቸው ለቦርዱ የሥራ ሂደትና ቦርዱ ያሉበትን ክፍተቶች በማወቅ በጊዜ መልሰ እየሰጡ ከመሄድ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል። ሰብሳቢዋ በመድረኩ ሊመለሱ የሚችሉትነ ጥያቄዎች መልስ የሰጡ ሲሆን፤ ከዚሀ በፊት እነደተናገሩት ጥያቄዎች በመድረክ ብቻ ሊወሠኑ እንደማይገባ ገልጸው መሠል መድረኮች ምርጫው እንደመቅረቡ መጠን በአጭር የጊዜ ርቀትና በተከታታይ እንደሚዘጋጁ አስታውቀዋል።

    

NEBE/CR

Share this post